Search

"ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆን አለበት"፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሙፈሪሀት ካሚል

ሓሙስ ጥቅምት 26, 2019 67

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 98 የተደነገገው የጋራ ገቢዎች አስተዳደርና ክፍፍል ሕገ መንግሥታዊ መብት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጡን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክትትልና በግምገማ ሥራዎቹ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሙፈሪሀት ካሚል አስታወቁ።

አፈ ጉባኤዋ ይህን ያመለከቱት እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትንና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴና የማኔጅመንት አባላት ጋር የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ባካሄዱበት ወቅት ነው።

የመደመር መንግሥት ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ ሳይሻሻል የቆየውን የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቀመር በ2012 ዓ.ም. በጥናት ላይ በተመሠረተ ግምገማ እንዲሻሻል ማድረጉ፣ መንግሥት የዜጎችን ተጠቃሚነት በተግባር ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ማረጋገጫ መሆኑን ወ/ሮ ሙፈሪሀት አብራርተዋል።

በተጨማሪም የምክር ቤቱ ዕቅድና አፈጻጸም ከታላቁ የመደመር ስትራቴጂ ጋር የተሰናኙና የተጣጣሙ መሆን እንዳለባቸው በመደበኛና በኢመደበኛ ግብረ መልስ እየፈተሹ መሄድ እንደሚገባ አፈ ጉባኤዋ ማሳሰባቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

ያሉትን በጎ መልካም ተሞክሮዎች በማስቀጠልና የሚታዩ ጉድለቶችን በማረም፣ በታላቁ የመደመር ስትራቴጂ የተቀመጠውን የተዋሃደች፣ አምራች፣ መሪ፣ ጽኑ እና የሠለጠነች ኢትዮጵያን እ.ኤ.አ በ2050 እውን የማድረግ ታሪካዊ ርዕይ ለማሳካት ሁሉም አመራርና ባልደረባ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 

በቀጣይም የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ዜጋ ተኮር ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል፣ የታላቁን የመደመር ስትራቴጂ ስኬት እውን ለማድረግ ምክር ቤቱ በትኩረት እንደሚሠራ ተመላክቷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: