Search

የሥልጣኔ ምንጭ፣ የዘመናዊነት ዐሻራ፦ በሕይወት ዘመን ልትጎበኝ የሚገባት ኢትዮጵያ

ረቡዕ ጥቅምት 25, 2019 41

በዓለም አቀፉ የቱሪዝም መድረክ አንድን ሀገር መጎብኘት አዲስ መልክዓ ምድር እና ባህል ከማየት ባለፈ ትርጉም ላይኖረው ይችላል፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግ ጉዞ ግን ከባዕድ ምድር ጋር መተዋወቅ ሳይሆን ወደ ራስ ማንነት እና ወደ ሰው ዘር መነሻ መመለስ ነው።

የቅድመ ሰው ዘር ጥናት (Paleoanthropology) መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት፣ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ እና የታሪክ መጀመሪያ ምዕራፍ የተጻፈባት ምድረ ቀደምት ናት።

በአፋር ስምጥ ሸለቆ የተገኘችው የ3.2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያላት ሉሲ (ድንቅነሽ)፣ የ4.4 ሚሊዮን ዓመቷ አርዲ እንዲሁም በመልካ ቁንጡሬ የተገኙት የ2.6 ሚሊዮን ዓመታት ዕድሜ ያላቸው የመጀመሪያዎቹ የድንጋይ መሣሪያዎች ኢትዮጵያ የሰው ልጅ የልደት ስፍራ መሆኗን በሳይንሳዊ መረጃ ያረጋግጣሉ።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሥልጣን ዘመናቸው ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት፣ በብሔራዊ ሙዚየም የሉሲን አጽም ከተመለከቱ በኋላ፣ “የዓለም ሕዝብ ሁሉ ከአንድ የዘር ግንድ ስለመመዘዙ ሉሲ ሕያው ማሳያ ናት፤ ኢትዮጵያ የቡና ብቻ ሳትሆን የሰው ዘር ሁሉ መገኛ ናት” በማለት የሰጡት ምስክርነት፣ ማንኛውም የዓለም ዜጋ ኢትዮጵያን መጎብኘቱ ወደ ቅድመ አያቶቹ ቀዬ የሚያደርገው ታሪካዊ መመለስ መሆኑን ያሳያል።

ይህ የቀደምትነት ጸጋ በቅሪተ አካላት ብቻ የተገደበ ሳይሆን በተፈጥሮ ሀብት እና በታሪካዊ ቅርሶችም የደመቀ ነው። ዓለም በየዕለቱ የሚነቃቃበት የአረቢካ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ በተፈጥሮ የበቀለባት እና ከ6 ሺህ በላይ የቡና ዝርያዎች የሚገኙባት ኢትዮጵያ፣ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ በዘርፉ ተሳታፊ ሲሆን ልዩ የቡና ሥነ ሥርዓቷም የክብር እና የእንግዳ ተቀባይነት መገለጫ ነው።

ለሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የሕይወት እስትንፋስ የሆነው የዓባይ ወንዝ መነሻው ጥንታዊ ገዳማትን እና የሥነ ሥዕል ቅርሶችን ያቀፈው የጣና ሐይቅ መሆኑ፣ ከዝቅተኛው የዳሎል አስደናቂ መልክዓ ምድር እስከ ብርቅዬዎቹ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮ እና ጭላዳ ዝንጀሮ መገኛ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ድረስ ያለው የተፈጥሮ ንጽጽር በዓለም ወደር የለውም።

በተጨማሪም በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት የአክሱም ሐውልቶች፣ ሕያው ቅርስ የሆኑት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጎንደር የፋሲለደስ ግንብ ከሀገራችን የባህል ብዝኃነት እና የታላላቅ አትሌቶች ዝና ጋር ተዳምረው ኢትዮጵያን በሕይወት ዘመን ልትጎበኝ የሚገባት ልዩ መዳረሻ ያደርጓታል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ጥንታዊ የሥልጣኔ ከፍታ ከዘመናዊው ዓለም ጋር ለማስተሣሠር እና ዳግም ለመገንባት እያከናወናቸው ያሉ ግዙፍ የልማት ሥራዎች ለቱሪዝም ዘርፉ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ እየተተገበሩ ያሉት የከተማ ማዘመን፣ የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች የመዲናዋን ገጽታ በአስደናቂ ሁኔታ ቀይረውታል። ሰፋፊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ዘመናዊ የመብራት እና የትራፊክ ሥርዓቶች ከተማዋን ውብ፣ ጽዱ እና ለጉብኝት ተመራጭ አድርገዋታል።

እንደ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ያሉ ታሪክን፣ ተፈጥሮን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያዋሀዱ ሜጋ ፕሮጀክቶች የመደመር እሳቤ የወለዳቸው የዘመኑ የሥልጣኔ አሻራዎች ናቸው።

እነዚህ ዘመናዊ የከተማ ልማት ውጤቶች ከሀገራችን ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ጋር ሲቀናጁ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ስትራቴጂያዊ አቅምን በእጅጉ አሳድገውታል።

የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ፣ ከኒውዮርክ እና ጄኔቫ ቀጥሎ የበርካታ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቦች መገኛ ናት።

ከተማዋ እንደ ሸራተን፣ ሂልተን፣ ራዲሰን ብሉ እና ስካይላይት ያሉ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች፣ ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሾች እና አፍሪካን ከዓለም ጋር የሚያስተሣሥረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰፊ የበረራ መረብ ባለቤት መሆኗ ለታላላቅ ጉባኤዎች ምቹ ያደርጋታል።

ዓለም አቀፍ ተቋማት በአዲስ አበባ ጉባኤዎቻቸውን ሲያካሂዱ፣ ተሳታፊዎች በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማቶች የተዋበችውን ዘመናዊት ከተማ ከማድነቅ ባሻገር፣ የሉሲን አጽም፣ የላሊበላን ጥበብ እና የጣናን ገዳማት መጎብኘት ይችላሉ።

የዓለም መሪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ባለሀብቶች ስለ ነገው የዓለም ዕጣ ፈንታ ለመምከር ከሰው ዘር መነሻ ከሆነችው እና በአዲስ የሥልጣኔ ምዕራፍ እየደመቀች ካለችው ኢትዮጵያ የተሻለ ስፍራ አያገኙም፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያ መሰባሰብ በታሪክ ምንጭ ላይ ቆሞ የወደፊቱን ዓለም መቅረጽ ነው።

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: