ኢትዮጵያ ሀገራዊ ዕድገቷን ለማፋጠንና የኢኮኖሚ መዋቅሯን ለማጠናከር በወጣቶች የሥራ ፈጠራ፣ የክህሎት ማደራጃና የመሪነት ተሳትፎ ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ይገኛል።
የዚህ ታላቅ ሀገራዊና አህጉራዊ ራዕይ አካል የሆነው ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የሴቶችና የወጣቶች የፖለቲካ አመራር ሚና ላይ ያተኮረ ምክክር እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) የበለፀገችና ጠንካራ አፍሪካን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የአህጉሪቱ ዋነኛ ጥንካሬ የሆኑት ወጣቶች በፖሊሲ አውጪነትና በመንግሥት ሥልጣን ደረጃ ንቁ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ ጠቅላላ ሕዝብ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ዕድሜው ከ25 ዓመት በታች እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ እነዚህ ወጣቶች የሰላም ግንባታና የሥራ ፈጠራ ግንባር ቀደም አንቀሳቃሾች በመሆናቸው ለአህጉሪቱ ዕድገትና ትስስር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ወጣቶች ነገን ብቻ ሳይሆን ዛሬንም የመምራት አቅም እንዳላቸው በማመን ረገድ አርአያ የሚሆን እርምጃ እየወሰደች እንደምትገኝ ተጠቅሷል።
በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት በመንግሥት የተለያዩ የአመራር እርከኖች ውስጥ በርካታ ኃላፊነቶች በወጣቶች ተይዘው ይገኛሉ።
ወጣቶች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ድምፅ ሰጪ ብቻ ከመሆን ተሻግረው በሚወጡ ፖሊሲዎች፣ በውሳኔ ሰጪነት እና በመንግሥት ሥልጣን ላይ በቀጥታ በመሳተፍ አህጉራዊና ሀገራዊ እድገትን እንዲያፋጥኑ ጥሪ ቀርቧል።
ሚኒስትሩ አክለውም ወጣቶች ብቁ እና የበቁ ሲሆኑ ሀገራትም በሁሉም ዘርፍ ብቁ እና ጠንካራ እንደሚሆኑ በመግለጽ፣ የወጣቶች ጥንካሬ የራሷ የአፍሪካ ጥንካሬ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ ጥረት ወጣቶችን የሀገር ባለቤት እና የውሳኔ ሰጪነት ማዕከል በማድረግ አፍሪካን ወደ ላቀ የብልጽግና ማማ ማዕረግ የሚያሸጋግር ሕያው እርምጃ ነው።
ወይንሸት ደጀኔ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: