Search

በመቐለ 5 ሺህ 500 የቀድሞ የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ገቡ

ሓሙስ ጥቅምት 26, 2019 73
በመቐለ የተሃድሶ ማዕከል 5 ሺህ 500 የቀድሞ የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ተሃድሶ ሥልጠና መግባታቸው ተገለጸ።
ሥልጠናው የተጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አመራሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ድጋፍ አድራጊ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በመርሐ-ግብሩ ላይ እንዳብራሩት፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ከ92 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት በመመለስ፣ አገራዊ ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን አከናውኗል።
በአሁኑ ወቅትም በትግራይ ክልል የሚገኙ በርካታ የቀድሞ ተዋጊዎች ግጭትን በመተው ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው ለመመለስ፣ በከፍተኛ ቁጥር ወደ ተሃድሶ ማዕከላት በመግባት በመልሶ ማቋቋም (DDR) ፕሮግራሙ ለመታቀፍ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑ ተመላክቷል ፌዴራል መንግሥት ባለድርሻ አካላት ጋር በከፍተኛ ቅንጅትና ትብብር እየተከናወነ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 525/2015 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፤ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የማሰናበት (Demobilize) እና ወደ ማኅበረሰቡ በዘላቂነት የመልሶ ማቋቋም (DDR) ሥራዎችን የሚያከናውን ተቋም ነው።
ኮሚሽኑ በተለይም በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በአፋር ክልሎች ለቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሩ እያደረገ ይገኛል።

 

 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: