Search

የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና አዲሷ አዲስ አበባ፤ ከኮሪደር ልማት እስከ አፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ

ሓሙስ ጥቅምት 26, 2019 69

የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻዎችና የኮሪደር ልማት ሥራዎች መዲናዋን ከማስዋብና ገጽታዋን ከመቀየር ባለፈ፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ፣ የትራንስፖርት እና የማኅበራዊ ዕድገት ቁመና በከፍተኛ ደረጃ ያሳደጉ ታሪካዊና መዋቅራዊ ፕሮጀክቶች ናቸው።

እነዚህ የተቀናጁ የልማት ሥራዎች የከተማዋ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ በማሳለጥና የከተማዋ መዋቅር ከዘመኑ ጋር እንዲራመድ በማድረግ ረገድ የማይተካ መሠረት ጥለዋል።

ከዚህ ቀደም የወንዝ ዳርቻዎች የቆሻሻ መጣያ፣ የመርዛማ ኬሚካሎች መድፊያ እንዲሁም ለጎርፍ አደጋ የተጋለጡ ነበሩ።

ዛሬ ላይ ግን በመልሶ ማልማት ሥራው እነዚህ ስፍራዎች ሙሉ በሙሉ ተለውጠው የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር የሚመጥኑ ውብ የመኖሪያ መንደሮች፣ አረንጓዴ መናፈሻዎችና ለመኖሪያ ምቹ አካባቢዎች ሆነዋል።

በእነዚሁ የመዲናዋ አካባቢዎች የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴውንና ንግዱን በከፍተኛ ደረጃ አፋጥነውታል።

ሰፊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ ዘመናዊ የመብራት ሥርዓቶችና ውብ አረንጓዴ ስፍራዎች መዲናዋን ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ተፊላጊ የመዝናኛ መዳረሻ አድርገዋታል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ለብዙዎች የሥራ ዕድል የፈጠረና የሀገር አቅምን ያሳደገ ሲሆን፣ አዲስ አበባ በከተማ ልማትና በአካባቢ ጥበቃ ያሳየችው ይህ ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ የ2024 የ“ሴኡል ከተማ ሽልማት” እና የ2026 የ“ሸንሃይ አዋርድ” አሸናፊ እንድትሆን አስችሏታል።

ይህ አረንጓዴ፣ ጽዱና ሰው ተኮር የልማት ተሞክሮ በአሁኑ ወቅት በክልል ከተሞችም በስፋት እየተገበረ ይገኛል።

በሌላ በኩል፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታውና የከተማዋ መዘመን አዲስ አበባን የአፍሪካ ዋና የኮንፈረንስ ቱሪዝም (MICE) ማዕከል አድርጎ አጉልቶታል።

ዘመናዊ የጉባዔ አዳራሾች፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የተቀናጀ የትራንስፖርት አቅርቦትና የላቀ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ከተማዋ ትልልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮችን በብቃት እንድታስተናግድ አስችሏታል።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭነቷንና ዲፕሎማሲያዊ ገጽታዋን ይበልጥ ያጠናከረችው አዲሷ አዲስ አበባ፣ ከዛሬ ጀምሮ 2ኛውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔን በእንግዳ ተቀባይነት ማስተናገድ ጀምራለች።

ይህ ታላቅ ሁነት ከተማዋ የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በተግባር ያረጋገጠችበት ሌላው ምዕራፍ ነው።

 

በማስተዋል መታፈሪያ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: