Search

የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀመረ

ረቡዕ ጥቅምት 25, 2019 39

የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን እንዲሁም አባል ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ተጀምሯል።

ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ስብሰባው ሁለቱ አህጉራት ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ለመመካከር እና የጋራ ፍላጎት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትብብሮችን ይበልጥ ለማጠናከር ቁልፍ መድረክ መሆኑ ተገልጿል።

ስብሰባው እ.አ.አ በኅዳር 2025 “ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በማጠናከር ሰላም እና ብልጽግናን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ሐሳብ በአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ የተካሄደው 7ኛው የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት ጉባኤ ውጤቶችን የበለጠ ለማጎልበት ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በሉዋንዳ ቃል ኪዳኖች መሠረትም መድረኩ በባለብዙ ወገን እና በብልጽግና ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን ያደርጋል። ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ በሰላም እና ፀጥታ፣ የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን ማጠናከር፣ ንግድ እና የኢኮኖሚ ልማት፣ የአየር ንብረት፣ የምግብ ዋስትና፣ የዲጂታል እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ልማት እንዲሁም በመልካም አስተዳደር መስኮች ተጨባጭ ውጤት የሚያስገኙ የትግበራ ዕቅዶች ላይም ይመክራል።

ይህ የትግበራ ዕቅድ “የጋራ ራዕይ 2030”ን እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063ን እና የአውሮፓ ኅብረት ‘ግሎባል ጌትዌይ’ን የመሳሰሉ ተያያዥ ማዕቀፎችን ለማጠናከር ያግዛል።

በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያ በዲጂታል እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አስተዳደር እና ልማት ዙሪያ የአፍሪካ ኅብረትን የጋራ አቋም አቅርባለች። አቋሙ የቀረበው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ኅብረት የሰው ሠራሽ (AI) እና የዲጂታል ጤና መሪ በሆኑበት ኃላፊነት መሠረት ነው።

በዚሁ መሠረት አምባሳደር ለምለም ፈስሐ ባቀረቡት መግለጫ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች አብራርተዋል። እነዚህም፦

•  አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ዲጂታላይዜሽንን የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት የፖሊሲ ቅድሚያ ትኩረት እንዲሆኑ ማድረግ፤

•  ሁለንተናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትን ዕውን ማድረግ፤

•  በሳይበር መሠረተ ልማት ላይ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት ማሳደግ፤

•  ለዲጂታል ስታርት-አፖች (አዳዲስ ቴክኖሎጂ ተኮር ሥራ ፈጣሪዎች) ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር፤

•  በአፍሪካ ቋንቋዎች ላይ ያተኮረ አሳታፊነትን ማጎልበት፣ እና

•  የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን አሉታዊ ተጽዕኖዎች የመቆጣጠር እና የማስተዳደር አቅምን መገንባት መሆናቸው ተብራርቷል።

በሌላ በኩል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) በተወከለችው ኢትዮጵያ፣ በንግድ፣ በኢነርጂ ልማት እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የአፍሪካን እና የአውሮፓን አጋርነት ማስፋፋት በሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ላይ አጽንኦት ሰጥታለች።

አምባሳደሩ የአውሮፓ ኅብረት “ከጦር መሣሪያ በስተቀር ሁሉንም ነገር” ለሚለውን የንግድ ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም የደን ጭፍጨፋን የማስቀረት ደንብ እና የካርቦን ድንበር ማስተካከያ ዘዴ (CBAM) የሚሉ ደንቦች በኮኮዋ፣ በቡና እና በሌሎችም ስትራቴጂያዊ የንግድ ዕቃዎች አምራቾች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረሱ በመሆናቸው ኅብረቱ ማሻሻያ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በኢነርጂው ዘርፍ የአውሮፓ ኅብረት በአፍሪካ ኅብረት-ፓይዳ (AU-PIDA) ማዕቀፍ ውስጥ በሚገኙ ፕሮጀክቶች ላይ ተጨባጭ ኢንቨስትመንት እንዲያደርግ መጋበዛቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: