41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ጉባዔ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
"የትምህርት ምዘናን ለማሸጋገር ጥራት ያለው ትምህርትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ " በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው 41ኛው የአፍሪካ ትምህርት ምዘና ዓመታዊ ጉባዔ፤ ከነሀሴ 19 እስከ ነሀሴ 23 2017 ለአምስት ቀናት የሚደረግ ይሆናል።
ጉባዔው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንዲሁም ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ በርካታ እንግዶች በተገኙበት የመክፈቻ ፕሮግራሙ ተከናውኗል።
በጉባዔው ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፥ ዓለም በየዕለቱ በፍጥነት ስልጣኔን ተከትላ በለውጥ ጎዳና ላይ ባለችበት በአሁን ወቅት፤ አፍሪካ የወደፊቷን በጥንቃቄ መስራት ይኖርባታል ነው ያሉት።
ስለ አህጉራችን መሰረታዊ እና ዘላቂነት ያለው ለውጥ መስራት ያለብን ዛሬ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ግብርናው ዘርፍ፣ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በትምህርት ተደራሽነት ባለፉት 5 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ማከናወኗን ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ አያይዘው እንደገለጹት በኢትዮጵያ በሁሉም አከባቢዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እኩል ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ ነው።
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዳሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዚህ ጉባዔ በትምህርትና ምዘናና ሥርዓት ዙሪያ ያሉ እሳቤዎች፣ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ልምዶች የሚቀርቡበት መድረክ ነው ብለዋል።
በምዘናና ፈተና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ፤ ዘላቂ የሆነ ትብብርን በመፍጠር በጋራ መስራት የጉባዔው ዋና አላማ መሆኑን አንስተዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ