Search

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትርጉም ያለው ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል - ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

ሰኞ የካቲት 30, 2018 52

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መንግሥት እና ሕዝብ የጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት እና ትርጉም ያለው ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) አሳሰቡ።

ትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የገባውን የ2018 ዓ.ም የቁልፍ ውጤቶች አመላካቾች ስምምነት አፈጻጸም በአዲስ አበባ አዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል እየገመገመ ይገኛል።

ተቋማቱ ከመማር ማስተማር ባለፈ የአካባቢያቸውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በጥናት እና ምርምር እንዲፈቱ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠይቀዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥም ከአመራር እስከ ታችኛው የሥራ ክፍል የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሸኔ እንዳሉት፣ ተቋማቱ በሥራ ባህል እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ መሻሻል ቢያሳዩም በቅንጅት የመሥራት ክፍተቶች ይታይባቸዋል። 

ይህንን የአመራር ችግር ለመቅረፍም “የአመራር አካዳሚ” እየተቋቋመ መሆኑን እና በቅርቡ ሥልጠና እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

ግምገማው ተቋማቱ ከሚኒስቴሩ ጋር በገቡት ውል መሠረት ያከናወኗቸውን ተግባራት እና ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በጥልቀት ለመለየት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በሰናይት ብርሃኔ

#Ethiopia #EducationReform #HigherEducation #AcademicExcellence #MoE