Search

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እና የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አባላት የማዕረግ ዕድገት ተሰጣቸው፤ 'ማዕረግ ከኃላፊነትና ከተጠያቂነት ጋር የሚሰጥ ክብር ነው'፦ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ

ማክሰኞ መጋቢት 01, 2018 48

በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የመቆያ ጊዜያቸውን አጠናቀው መሥፈርቱን ላሟሉ አባላት የማዕረግ ማልበስ መርሃ-ግብር አካሂዷል።
በዕለቱ ማዕረግ ያለበሱት የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ባስተላለፉት መልእክት፤ የማዕረግ ሹመት ከከፍተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ጋር አብሮ የሚሰጥ ክብር መሆኑን ገልጸዋል።
ወታደር ላሳለፈው የትግል ውጣ ውረድ፣ ላሳየው የዓላማ ጽናትና መልካም ዲሲፕሊን የሚሰጠው ይህ ሹመት፣ የመምራት አቅምንና የመፈጸም ብቃትን ይበልጥ ሊያሳድግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ተሿሚዎችም የተሰጣቸውን ተጨማሪ ኃላፊነት በመረዳት፣ በቀደሙ የውጊያ ተሞክሮዎች ታግዘው ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የመከላከያ ዋር ኮሌጅ የ4ኛ ዙር መደበኛ ተማሪዎችና የስታፍ አባላት የማዕረግ ዕድገት አግኝተዋል።
የኮሌጁ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጥላሁን ደምሴ እንደገለጹት፤ የውትድርና ሙያ የሕይወት መስዋዕትነትን የሚጠይቅና ቅድሚያ ለሕዝብና ለሀገር የመቆም ተግባር በመሆኑ፣ ተሿሚዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለሀገራቸው ላቀ አገልግሎት እንዲያውሉት ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማህበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል።