Search

"የሀገርን ሀብት በራስ ዓይን ማየት መስታወት የመመልከት ያህል ነው" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ማክሰኞ መጋቢት 01, 2018 39

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን መልካ በሎ ወረዳ የሚገኘውን ታሪካዊውን የናሲኦል ዋሻ በጎበኙበት ወቅት፤ የሀገርን የተፈጥሮ ጸጋና ታሪክ በራስ አይን መመልከት እውነተኛ ማንነትን ለማወቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገርን ታሪክ በሌሎች መነጽርና ትርክት ብቻ መመልከት እውነተኛ ማንነትን እንደሚሸፍን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከውጭ የሚነገረን ትረካ እውነተኛ ማንነታችንን ስለማይገልጸው እውነተኛው ታሪካችን ሊታይ የሚችለው ዜጎች በተገለጠ አይንና በበራ አእምሮ የራሳቸውን ሀብት ማየት ሲችሉ ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ናሲኦል ዋሻ ከባሌ አዋሳኝ ወረዳዎች ጋር የሚቀራረብና አካባቢው በጥንት ዘመን የነበረን ከፍተኛ ስልጣኔና እውቀት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል።

የጥንት ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር ተዋህደው እንዴት ይኖሩ እንደነበርና ምን አይነት የላቀ አስተሳሰብ እንደነበራቸው ለማወቅ ቆም ብሎ ማጥናት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ለዚህም ምሁራን፣ አዋቂዎችና ሀገር ወዳድ ዜጎች መሰል የታሪክ ስፍራዎች ድረስ በመሄድና በመድከም የሀገራቸውን ሀብት በትክክለኛ መንገድ እንዲያጠኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ጉብኝት የኢትዮጵያን ያልተነኩ የታሪክና የተፈጥሮ ሀብቶች ለዓለም ለማስተዋወቅና ለትውልድ ለማቆየት የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑንም አመልክተዋል።

በቢታንያ ሲሳይ

#EBC #Ethiopia #AbiyAhmed #NasiolCave #EastHararghe #EthiopianHistory #Heritage