በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የኅብረቱ ሊቀመንበርና የአንጎላ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዦአዎ ሎሬንዞ፤ አፍሪካ ተግዳሮቶቿን ወደ ዕድል ለመቀየር አስፈላጊው ሀብት፣ እውቀትና ፖለቲካዊ አቅም እንዳላት ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው፤ አጋሮቻችን ለድምፃችን ትኩረት የሚሰጡት አህጉሪቱ ያላትን ሰፊ አቅም፣ የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሰላም፣ ኢኮኖሚና አየር ንብረት ጉዳዮች ላይ የምታንጸባርቀውን ሚዛናዊ የፖለቲካ አቋም ስለሚገነዘቡ ነው ብለዋል።
"የምንኖረው በዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካዊ መልሶ ማዋቀር ዘመን ውስጥ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በጤና፣ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም በምግብ ዋስትና ዙሪያ የጋራ አቋም እንድትይዝ እንደሚያስገድዳት አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ የአስተዳደር ተቋማት መዳከማቸውን የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ሎሬንሶ፤ ይህ ተጋላጭነት በአፍሪካ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመመከት የሕዝቦችንና የሀገራትን ጥቅም የማስጠበቅ ጥረት በእጥፍ ሊያድግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አፍሪካ ተግዳሮቶቿን ወደ ዕድል ለመቀየር አስፈላጊው ሀብት፣ እውቀትና ፖለቲካዊ ፍላጎት እንዳላት የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የሚያስፈልገው ወጥ የሆነ እርምጃና በኅብረቱ አባል ሀገራት መካከል ያለ አብሮነት መሆኑን አስረድተዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ