Search

የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ዘጠነኛ ቀንና ዓለም አቀፍ አንድምታው

እሑድ የካቲት 29, 2018 101

በመካከለኛው ምስራቅ በአሜሪካ-እስራኤል ጥምር ኃይሎች እና በኢራን ወታደራዊ ክንፎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ዛሬ 9 ቀኑን ይዟል።

ግጭቱ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ ወታደራዊ እርምጃዎች ተጠናክረው የቀጠሉበትና ዓለም አቀፍ ስጋት የነገሰበት ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

ባለፉት 48 ሰዓታት የጥምር ኃይሉ ጥቃቶች በኢራን የኃይልና የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማት ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በዋና ዋና ከተሞች የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ተከስቷል።

በሌላ በኩል፣ የኢራን ወታደራዊ ክንፎች በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የሚሳኤልና የድሮን ጥቃቶችን በመሰንዘር አጸፋዊ እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑ ተዘግቧል።

ግጭቱ ወደ ሊባኖስና ኢራቅ እየተስፋፋ መምጣቱ እንዲሁም በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ የተደቀነው ስጋት የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በአንድ ሳምንት ውስጥ 27 በመቶ እንዲንር ማስቻሉ ይገለፃል። የንግድ መርከቦችም ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የጉዞ መስመራቸውን እየቀየሩ ይገኛሉ።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወታደራዊ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሲገልጹ፤ የኢራኑ ፕሬዚዳንት ፔዜሽኪያን በበኩላቸው ሀገራቸው ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ራሷን የመከላከል መብቷን እንደምትጠቀም አስታውቀዋል።

በኢራን በኩል ለቀድሞው የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ተተኪን የመሰየሙ ሂደት መጠናቀቁንና ስምምነት ላይ መደረሱን የሀገሪቱ የባለሙያዎች ምክር ቤት ፍንጭ ሰጥቷል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውጥረቱ ወደ ከፋ ቀጣናዊ ጦርነት እንዳያመራ በስጋት እየተከታተለው ይገኛል።

#EBC #MiddleEastCrisis #GlobalImpact #EnergySecurity #Geopolitics #InternationalRelations