ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሠራዊት ማኅበር ወቅታዊ በሆነው የሀገሪቱ የባሕር በር አጀንዳ ላይ የፓናል ውይይት አካሄደ።
በውይይቱ ላይ የማኅበሩ አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ብርሃኑ አማረ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ የባሕር በር ጉዳይ ሀገራዊ አጀንዳ እንዲሆን በማድረጋቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።
"ኢትዮጵያና ቀይ ባሕር ተነጣጥለው አያውቁም" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በታሪክ አጋጣሚ የታጣውን የባሕር በር ጥያቄ ከዳር ለማድረስ ማኅበሩ ከኢትዮጵያውያን ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ማኅበሩ ይህንኑ አጀንዳ በማንገብ በሀገሪቱ በሚገኙ ከ300 በላይ ቅርንጫፎቹ ውይይቶችን እንደሚያስቀጥልና የመንግሥትንና የሕዝብን ፍላጎት ለማሳካት በልማትና በጸጥታ ሥራዎች ላይ በንቃት እንደሚሳተፍ አስታውቋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮነን በበኩላቸው፤ "ኢትዮጵያና ቀይ ባሕር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው" በማለት የሁለቱን ቁርኝት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር የመጠቀም መብቷ ሊረጋገጥ እንደሚገባ የገለጹት ጄኔራሉ፤ ይህም ከሀገራዊ ልማት ባለፈ ለቀጠናው ሰላም መረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በጋራ ተጠቃሚነትና ዲፕሎማሲን በሚያጠናክር መልኩ የቀረበ መሆኑን ያስታወሱት ጄኔራል ይመር፤ ማኅበሩ ይህንን ጉዳይ የህልውና አጀንዳ አድርጎ በመነሳቱ ምስጋና አቅርበዋል።
በዕለቱ በባሕር በር ጉዳይ ላይ የተለያዩ የመወያያ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ምክክር ተደርጎባቸዋል።
በመሐሪ አለሙ