Search

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከኅብረተሰቡ መረጃ የሚቀበልበትን የኮምዩኒኬሽን ፕላትፎርም ይፋ አደረገ

ረቡዕ የካቲት 25, 2018 54

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከኅብረተሰቡ መረጃ የሚቀበልበትና ሌሎችም የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጥ የኮምዩኒኬሽን ፕላትፎርም ይፋ አድርጓል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢቢሲ በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ በተቋሙ የውስጥ አቅም የበለፀገው ከመደበኛው ድረ-ገጽ በብዙ ገፅታዎቹ የሚለየው የኮምዩኒኬሽን ፕላትፎርም ዜጎች በፀጥታ፣ በደኅንነትና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ከየትኛውም ስፍራ ሆነው መረጃ የሚሰጡበት የሪፖርት ማድረጊያ ክፍል አለው ብሏል፡፡

ፕላትፎርሙ ሀገራዊ የደኅንነት፣ የመረጀና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተም  ወቅታዊ መረጃዎችን እንደሚያጋራ ተገልጿል፡፡

የኮምዩኒኬሽን ፕላትፎርሙ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ  የስጋት ተጋላጭነትን የተመለከቱ  የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች የሚሰጥ መሆኑን ያመለከተው አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ፤ በዚህም ኅብረተሰቡም ሆነ የውጭ ዜጎች መረጃውን በመጠቀም በየትኛውም ስፍራ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማገዝ ከፍተኛ ሚና ያበረክታል ብሏል፡፡

ፕላትፎርሙ ለወደፊቱ የተቋሙን መስፈርት የሚያሟሉና ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው ዜጎች አገልግሎት መሥሪያ ቤቱን በመቀላቀል ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የሚያስችል የማመልከቻ ገጽ የተካተተበት እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

የኮምዩኒኬሽን ፕላትፎርሙ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ እያከናወነ በሚገኘው ሪፎርም ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ በማበልፀግ የላቀ የመፈፀም አቅም ያለው ተቋም ለመገንባት የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑንም መረጃው ጠቁሟል፡፡ 

ዜጎችም ተዓማኒነት ያላቸውና ተጨባጭ መረጃዎችን በማጋራት የኢትዮጵያን የብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎች ለማሳካት  የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቋል፡፡

የኮምዩኒኬሽን ፕላትፎርሙ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የደኅንነት ተጋላጭነት ፍተሻ ተደርጎለት የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደተሰጠው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት  ለኢቢሲ የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

#EBC #Ethiopia #NationalSecurity #NISS #DigitalPlatform #CyberSecurity