ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማዎች ለማዋል በምታደርገው ጥረት፣ በዘርፉ ሰፊ ተሞክሮ ካላት አርጀንቲና ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግራለች።
በኢትዮጵያ የአርጀንቲና አምባሳደር ኢግናሲዮ ሮካታግሊያታ በአዲሱ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን (ENEC) ዋና መሥሪያ ቤት ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ ከኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ ጋር በሁለትዮሽ የትብብር መስኮች ላይ ዝርዝር ውይይት አካሂደዋል።
ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ አርጀንቲና በኒውክሌር ኃይል ማመንጫ፣ በምርምር ሪያክተር ዲዛይንና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ያላትን የዳበረ ተሞክሮ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያም ይህንን ዓለም አቀፍ ዕውቀት ለራሷ የኒውክሌር መርሃ ግብር ልማት ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
ሁለቱ ወገኖች በቴክኖሎጂ ትግበራ፣ በሰው ኃይል ልማት፣ እንዲሁም በጥብቅ የቁጥጥርና ሕጋዊ ማዕቀፎች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።
ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀና ዘላቂነት ያለው የኒውክሌር ፕሮግራም ለመገንባት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ታላቅ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።
ትብብሩ ሀገሪቱ በኢነርጂ እና በምርምር ዘርፍ የጀመረችውን የፈጠራ ጉዞ ይበልጥ እንደሚያፋጥነው ይጠበቃል።