Search

“ሴቶችን በየዘርፉ ማሳተፍ ሀገርን እንደ ማሳተፍ ይቆጠራል” - ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው

እሑድ የካቲት 08, 2018 128

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በ30ኛው የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ተቋም (OAFLAD) ጉባኤ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።
ቀዳማዊት እመቤቷ በንግግራቸው፤ የዘንድሮው የ30ኛው የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ተቋም ጉባኤ "የአፍሪካን ሴቶች ፈተናዎችን የመቋቋም ዐቅም መገንባት፡- የአየር ንብረት፣ ግጭቶች እና ዘላቂ ነገ” በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱን ገልጸዋል።
ይህ መሪ ቃልም በጾታ እኩልነት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ ዘርፍ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የአፍሪካ ሴቶችን ዐቅም ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ የማኅበራዊ ልማት ተግባራት የሴቶችን ዐቅም እንደሚያጎለብቱ የገለጹት ቀዳማዊት እመቤቷ፤ ይሄንን ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ቀዳማዊ እመቤት ጽሕፈት ቤት ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 37 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የሴቶችንና የሕፃናትን የትምህርት ተደራሽነት ለማሳደግ መሥራቱን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ለሴቶች የሙያና የንግድ ክሂሎት ሥልጠና፣ የመሥሪያ ቦታ፣ ግብዓትና የመነሻ ካፒታል በማመቻቸት ሴቶች በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት እንዲቀይሩ ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።
ሴቶችን በየዘርፉ ማሳተፍ ሀገርን በሙሉ እንደ ማሳተፍ ይቆጠራል ያሉት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ፤ ለኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ስኬት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በፈቃደኝነት ያደረጉት ተሳትፎ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአየር ንብረት መዛባትን ለመቋቋምም ሆነ ሌሎችንም የአፍሪካ ችግሮች ለመቅረፍ ሴቶች ወሳኙን ቦታ የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ያሳሰቡት ቀዳማዊት እመቤቷ፤ ለዚህም ስኬት ቀዳማዊ እመቤቶች ከፍ ያለ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።