Search

ሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት በዜጎች እጅ

ረቡዕ የካቲት 04, 2018 83

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዓለም አዲስ ታሪክ እየጻፈች ነው፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከፖሊስ አገልግሎት ጋር በማቀናጀት በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት በይፋ አስጀምራለች።
ይህ ዘመናዊ የዲጂታል ሥርዓት ዜጎች ምስልን፣ የጽሑፍ መልዕክትን፣ ተንቀሳቃሽ ምስልን (ቪዲዮ) እና ሌሎች ሰነዶችን በቀጥታ ለፖሊስ እንዲልኩ እንደሚያስችላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ኦፕሬሽን ዋና ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር አንድነት ሲሳይ ገልጸዋል።
ይህም ዜጎች ያለ ምንም እንግልት ፈጣን እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል።
የዜጎችን ደህንነት ጠብቆ በአፋጣኝ ምላሽ በሚያሰጠው በዚህ ቴክኖሎጂ፣ ሪፖርት የሚደረጉ ጉዳዮች እስከ ከፍተኛ አመራሮች ድረስ የሚታዩበት ስለመሆኑ ኃላፊው ለኢቢሲ ዶት ስትሪም አስረድተዋል።
በዋና ኦፊሰሮች ዕይታ ሥር በሆነው የስቴሽኑ ኪዮስክ (Kiosk) የሚቀርበው ቅሬታ፣ በቀጥታ ስርጭት ወደ ዋና ማዕከል ተላልፎ ለወንጀል መከላከል፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ለምርመራ እና ወደ ሌሎችም መዋቅሮች የሚመራ ይሆናል።
ይህን ተከትሎ ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል መልዕክት እንደሚደርሳቸው የገለጹት ኢንስፔክተር አንድነት ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በሶማሊኛ፣ በአፋርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂውን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ታይቶ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም ተሠርቷል።
ወደ ዲጂታል 2030 የምትገሰግሰው ኢትዮጵያ፣ ሰላም እና ደህንነት ለማስፈን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን እውን በማድረግ ሉዓላዊነቷን እንደምታስከብር ኢንስፔክተር አንድነት ተናግረዋል።
በአፎሚያ ክበበው