በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሚገኙ እና ለሺህ ዓመታት ሳይነኩ የቆዩ የተፈጥሮ እና የታሪክ ሀብቶች እንዲሁም ዋሻዎች በባለሙያዎች ጥልቅ ጥናት ሊደረግባቸው እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዞኑ የሚገኙ ከሺህ ዓመታት በፊት የነበሩ በርካታ ዋሻዎችን እና የተፈጥሮ መስህቦችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ እስከ 500 ሜትር ድረስ በዋሻው ውስጥ መጓዛቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እስከ 30 ሜትር ስፋት ያለውን ሥፍራ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ነጭ የእምነበረድ ዓይነት፣ የኖራ ድንጋይ እና ግራናይት የሚመስሉ የተለያዩ ማዕድናት ድብልቅ ያላቸውን ድንጋዮች መመልከታቸውንም ገልጸዋል።
"እነዚህ ቦታዎች እንዴት ተፈጠሩ? ሰዎችስ ምን ሚና ነበራቸው?" የሚለው ጉዳይ በሙያተኞች ዕውቀት እና በጠራ መረጃ ላይ የተመሠረተ ሰፊ ጥናት እንደሚፈልግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ምሥራቅ ሐረርጌ በዱር ፈረሶች፣ ዝሆኖች፣ ፍል ውኃዎች እንዲሁም እንደ ማርብል እና ግራናይት ባሉ ውድ ድንጋዮች የበለጸገች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
የሶማሊ እና የሐረሪ ክልሎችን ጨምሮ ቀጠናው መሠረተ ልማት ቢሟላለት፣ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ልማትና ሀብት ሊቀየሩ የሚችሉ እምቅ አቅሞች እንዳሉትም አስረድተዋል።
በላሉ ኢታላ