Search

ለስኬታማ ምርጫ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱት እነ ማን ናቸው?

ሰኞ የካቲት 30, 2018 58

የአንድ ሀገር ምርጫ ስኬታማ የሚሆነው የተለያዩ አካላት በቅንጅት እና በኃላፊነት ሲንቀሳቀሱ ነው።

በምርጫው ሒደት ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱት እነ ማን ናቸው? የሚጠበቅባቸው ተግባራትስ ምንድን ናቸው?

መራጩ ሕዝብ

የሥልጣን ምንጭ እና የመጨረሻው ወሳኝ አካል ሕዝቡ ነው። ከሕዝብ የሚጠበቅበት ተግባር በንቃት መመዝገብ፣ የፓርቲዎችን አማራጭ በጥልቀት መመርመር፣ ያለምንም ተፅዕኖ በነፃነት ድምፅ መስጠት እና ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አሉባልታዎችን በጥንቃቄ መመልከት ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ዕጩዎች

እነዚህ የውድድሩ ተዋንያን ናቸው። የሚጠበቅባቸው ተግባር የምርጫ ሕግን ማክበር፣ የፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸውን ለሕዝብ ማስተዋወቅ፣ ደጋፊዎቻቸው ሰላማዊ እንዲሆኑ ማስተማር እና የሕዝብን ውሳኔ በፀጋ መቀበል።

የምርጫ አስፈጻሚ አካል (ምርጫ ቦርድ)

ይህ አካል የምርጫው "ዳኛ" ነው፤ ገለልተኛ፣ ነጻ እና ታማኝ መሆን ይኖርበታል።

የሚጠበቅበት ወሳኙ ነገር ፍትሐዊ የድምፅ አሰጣጥ ሒደትን ማመቻቸት፣ የምርጫ ቁሳቁሶችን በወቅቱ ማቅረብ፣ የዕጩዎችን ምዝገባ ማከናወን እና ውጤቱን በግልፅነት ማሳወቅ።

ሲቪል ማኅበረሰብ እና የምርጫ ታዛቢዎች

እነዚህ አካላት የምርጫውን ተዓማኒነት የሚያረጋግጡ የገለልተኛ ወገን ምስክሮች ናቸው። ተግባራቸውም የምርጫውን ሒደት በቅርበት መከታተል፣ ግድፈቶች ካሉ ሪፖርት ማድረግ እና ለሕዝቡ የምርጫ ትምህርት መስጠት ነው። 

የመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያ) 

ሚዲያ የዲሞክራሲ ምሰሶ ነው። ለምርጫ ሂደት ስኬታመነት የሚጠበቅበት ተግባር ለሁሉም ተወዳዳሪዎች እኩል የአየር ሰዓት መስጠት፣ ትክክለኛ እና ያልተዛባ መረጃ ማሰራጨት እና ሕዝቡን የግንዛቤ ባለቤት ማድረግ ነው። 

የፀጥታ አካላት እና የፍትሕ ተቋማት 

እነዚህ አካላት የአጠቃላይ ሒደቱ ዘብ ናቸው፤ የሚጠበቅባቸው ተግባር ደግሞ የፀጥታ አካላት የምርጫውን ሰላማዊነት ያለአድልዎ ማስከበር ነው። የፍትሕ ተቋማት (ፍርድ ቤቶች) ደግሞ ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚነሡ ቅሬታዎችን በፍጥነት እና በፍትሐዊነት የመዳኘት ኃላፊነት አለባቸው።

ምርጫ አንድ ሒደት እንጂ የአንድ ቀን ክስተት አይደለም። ለምርጫ ውጤታማነት እነዚህ ሁሉ አካላት ተናብቦ መሥራት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። 

በዮናስ በድሉ

#Ethiopia #elections #7thgeneralelection #EBC #ebcdotstream