Search

የኢትዮጵያ ተቋማዊ የዴሞክራሲ ጉዞ እና የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 86

የፖለቲካ ተሳትፎን ማስፋት፣ የተለያዩ የፖለቲካ አማራጮችን ማበረታታት እና ተቋማዊ ዴሞክራሲን ማጠናከር የአንድ ሀገር የፖለቲካ ሥርዓት ብስለት ከሚለካባቸው ዋና ዋና መስፈርቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም ከተካሄደው ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ በኋላ በመደመር እሳቤ በፖለቲካ ምኅዳሯ፣ በምርጫ ተቋሟ ተዓማኒነት እና በፓርላማዊ ውክልናዋ ስብጥር ላይ ጉልህ ለውጦችን አስተናግዳለች።

በተለይም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የፓርቲዎች ውክልና መስፋፋት ሀገራችን የጀመረችውን ተቋማዊ የዴሞክራሲ ግንባታ እመርታ አመላካች ነው።

አዲስ አበባ እያስተናገደችው ያለው አህጉራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ ደግሞ በአህጉር ደረጃ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለማካፈል ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

ሀገራችን በመደመር መንግሥት መሪነት የተገደበ የፖለቲካ ምኅዳርን እና የፖለቲካ ውጥረቶችን በመስበር አዲስ አቅጣጫ ጀምራለች።

የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፣ በውጭ ሀገር የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ መደረጉ እና የመደመር አስተሳሰብ ልዩነቶችን በውይይት እና በመተባበር ለማስተናገድ ያቀረበው እሳቤ ለፖለቲካ ባህሉ መታደስ ትልቅ መሠረት ጥሏል።

የፖለቲካ ምኅዳር መከፈቱን ለማረጋገጥ ደግሞ የምርጫ ተቋም ነፃነት እና ተዓማኒነት ወሳኝ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 በተደረጉ ተቋማዊ ማሻሻያዎች አደረጃጀቱን እና የአባላቱን ስብጥር ግልጽ እና በሙያዊ ብቃት ላይ የተመሠረተ በማድረግ ተዓማኒነቱን አጠናክሯል።

ይህ ተቋማዊ ማሻሻያ ፍሬ ያፈራበት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮችን ያሳተፈ ታሪካዊ ክስተት ነበር።

በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ተወክለው የነበረ ሲሆን፣ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግን ይህ ቁጥር ወደ 18 ፓርቲዎች ከፍ ማለቱ የምክር ቤቱን የፖለቲካ ስብጥር አሳድጎታል።

ከሀገር ውስጥ ተቋማዊ ለውጥ ጎን ለጎን፣ ኢትዮጵያ የአህጉራዊ የፖለቲካ ውይይት ማዕከልነቷን አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2019 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ የዚህ ማሳያ ነው።

በብልጽግና ፓርቲ አዘጋጅነት እና ‘ከአፍሪካ ገቨርናንስ ሴንተር’ ጋር በመተባበር “ዕድገትን መምራት፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መፃኢ የኢኮኖሚ መሐንዲሶች” በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀው በዚህ ጉባኤ ከ20 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የፓርላማ አባላት፣ ሚኒስትሮች እና ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።

የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከምርጫ ውድድር እና ከሥልጣን ፉክክር ባለፈ በሀገራዊ ግንባታ፣ በረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በኢንዱስትሪ ልማት እና በአህጉራዊ ትሥሥር ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረጊያ መድረክ መፍጠር ነው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ይህንን አህጉራዊ ጉባኤ ማስተናገዷ፣ የራሷን የፖለቲካ ለውጥ እና የመደመር አስተሳሰብ ተሞክሮ ለአፍሪካውያን ወንድሞቿ የምታካፍልበት እንዲሁም ከሌሎች ተሞክሮ የምትማርበት ታላቅ ዕድል ነው።

በምርጫ ተቋማት ማሻሻያ እና በፓርላማዊ ውክልና መስፋፋት የተጀመረው ሀገራዊ የዴሞክራሲ ጉዞ፣ የፖለቲካ ልዩነት የሀገር ድክመት ሳይሆን ለሀገር ግንባታ የሚውል አቅም መሆኑን በተግባር በማረጋገጥ ዘላቂ እና ውጤታማ የዴሞክራሲ ሥርዓትን እውን የማድረግ ራዕዩን አጠናክሮ ይገፋበታል።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: