Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው ሁለቱ ዋና ዋና ምክረ ሐሳቦች

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 121

በሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ መድረክ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በሚጸድቀው ‘የአዲስ አበባ የአቋም መግለጫ’ ውስጥ እንዲካተቱ አህጉራዊ ፋይዳ ያላቸውን ሁለት ታላላቅ ሐሳቦች ለአፍሪካ የፖለቲካ መሪዎች አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የመጀመሪያው ጥሪ፤ “ከምርጫ ውድድሮች ባሻገር የሚጸኑ ሀገራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ግቦች ላይ መስማማት” የሚል ነው።

ገዢ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫ ፉክክር በኋላም የማይቀየሩ እና ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገሩ የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ግቦች ላይ የጋራ ስምምነት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖሊሲ አፈጻጸም፣ ወጪ እና ውጤታማነት ላይ የቅርብ ክትትል እያደረጉ ሀገራዊ አጀንዳዎችን መደገፍ እንደሚገባቸው ነው ያስረዱት።

ሁለተኛው ደግሞ “አዲሱን ትውልድ ለፖለቲካ አመራርነት ማዘጋጀት” የሚል ነው። በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ብቁ ተኪ መሪዎችን ባለማዘጋጀታቸው ምክንያት የልማት ግቦቻቸው እና ጉዟቸውን እንደሚያጡ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለወጣቶች እውነተኛ ኃላፊነት መስጠት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአመራር ልሕቀት አካደሚን በሮች ለአህጉሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክፍት በማድረግ እና ሥልጠናዎችን በመስጠት ለአህጉራዊ የአመራር ዕድገት የበኩሏን አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን እና ወደ ፊትም ይህንኑ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የፖለቲካ መሪዎች በሚቀጥለው ስብሰባ ሲገናኙ እያንዳንዱ ፓርቲ ከዚህ መድረክ ከተማረው ትምህርት ተነሥቶ በሀገሩ ላይ ያመጣውን አንድ ተጨባጭ ለውጥ ሪፖርት የሚያደርግበት አሠራር እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: