Search

መደመር መከፋፈልን አሸንፎ ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚገነባ የጋራ ቤታችን ነው፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 85

በአዲስ አበባ በታሪካዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ በሚገኘው 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች አህጉራዊ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪዎች የተውጣጣ አዲስ የመደመር መንግሥት ማቋቋሙን ተናግረዋል።

“እድገትን መምራት፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መፃኢ የኢኮኖሚ መሃንዲሶች” በሚል መሪ ሐሳብ በብልፅግና ፓርቲ አዘጋጅነትና በአፍሪካ ገቨርናንስ ሴንተር አስተባባሪነት እየተካሄደ ባለው አህጉራዊ መድረክ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመደመር ፍልስፍናን፣ የፓርቲያቸውን የሪፎርም ጉዞ እና የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ባህል ለማሳደግ የተወሰዱ ውሳኔዎችን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።

በ2018ቱ ጠቅላላ ምርጫ በፓርላማ ውስጥ ካሉት መቀመጫዎች 15 በመቶ ያህሉ እጩዎችን ላለማቅረብ በመወሰን ተፎካካሪዎች እንዲሳተፉ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው የመደመርን አስተሳሰብ ሲያብራሩ "መደመር (አብሮነትና ኅብረት) ማለት ሲሆን የሕዝባችንን የተለያዩ ጥንካሬዎች ለጋራ ዓላማ ዙሪያ የምናሰባስብበት መርሃችን ነው" ብለዋል።

የተለያዩ ክልላዊ መሠረት የነበራቸውን ድርጅቶች ወደ አንድ ብሔራዊ ፓርቲ ማዋሃዳቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት ብልፅግና ወደ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት ያሉትና እያንዳንዱ አባል ለአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ኃላፊነት የሚወስድበት መዋቅር መገንባቱን ገልጸዋል።

መሪዎች ልክ እንደማንኛውም ዜጋ ተመሳሳይ ደንቦችን መከተል እንዳለባቸው እና ውጤቶች በየጊዜው እንደሚገመገሙም ጠቁመዋል።

ከእነሱ ጋር የማይስማሙትን አካላት በግልጽነት ማስተናገድ ከባድ ፈተና መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እያንዳንዱ ዜጋ የትኛውንም ፓርቲ ቢደግፍ በሀገሩ ላይ እኩል መብት እንዳለው አስምረውበታል።

የፖለቲካ መሪዎች የሚወስዷቸው ውሳኔዎች በዜጎች ዕለታዊ ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሕዝብን እምነት ላለማጣት የፖለቲካ ፓርቲዎች በቃላት ሳይሆን በሥራና በውጤት ማረጋገጥ እንዳለባቸው አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብን ፍላጎት ለማሟላት አስቸጋሪ የሚባሉ የኢኮኖሚ ውሳኔዎችን እየወሰደ እንደሚገኝና ዋናው ዓላማም ለንግድ ድርጅቶች፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለማምረት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሰፊ ክፍተት መስጠት መሆኑን አብራርተዋል።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: