Search

የመደመር መንግሥት የዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት የመለወጥ ጉዞ

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 169

የፖለቲካ አስተሳሰቦች፣ ርዕዮተ ዓለሞች እና የመንግሥታት ፖሊሲዎች እውነተኛ ፋይዳ የሚለካው፤ በሚተላለፉ ውሳኔዎች፣ በሚወጡ መመሪያዎችና በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በበጎ መልኩ መቀየር ሲችሉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ እና የመንግሥት ውሳኔ ትክክለኛ መለኪያ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት ማሻሻል መቻሉ ነው" በማለት በሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ ያስተላለፉት መልዕክት፣ የፖለቲካ ሥልጣንና የአመራር ሚና የመጨረሻ ግብ ምን መሆን እንዳለበት ግልጽ ያደረገ መርህ ነው።

የመደመር መንግሥት ይህንን መርህ መሬት ለማስረገጥ እና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ባለፉት ዓመታት በርካታ ሀገራዊ እና ማኅበራዊ ፕሮግራሞችን ቀርጾ በቁርጠኝነት በመተግበር ላይ ይገኛል።

የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት መሠረት አንዱ የምግብ ዋስትና በመሆኑ የመደመር መንግሥት በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበው የመስኖ ስንዴ ልማት ውጤት ኢትዮጵያን ከስንዴ አስመጪነት ወደ ላኪነት ያሸጋገረ ትልቅ ስኬት ነው።

ይህ ተግባር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጡ ባለፈ፣ የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ላይ በቀጥታ በጎ ተፅዕኖ አሳድሯል።

በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገራችን ክልል ከተሞች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ የከተሞችን ውበት ከማስጠበቅ ባለፈ የዜጎችን የመኖርያ አካባቢ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ምቹ አድርጓል።

በዚህም ለዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል የሚገነቡ አዳዲስ መኖሪያ ቤቶች፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ መሠረተ ልማቶች፣ አረንጓዴ እና የመዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ተግባራት የከተማ ነዋሪውን የዕለት ተዕለት የኑሮ ጥራት በቀጥታ ያሻሻሉ አዎንታዊ እርምጃዎች ናቸው።

በተጨማሪም  የማዕድ ማጋራት፣ የአረጋውያን እና የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራሞች፣ የመንግሥት ውሳኔዎች እስከ ዝቅተኛው ማኅበረሰብ ድረስ መድረሳቸውን ያረጋገጡ ናቸው።

ይህም የፖለቲካ ውሳኔዎች በወረቀት ላይ ብቻ ሳይቀሩ የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ማረጋገጥ እንዳለባቸው የሚያሳይ ተግባራዊ ማረጋገጫ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተጀመረው "የአረንጓዴ ዐሻራ" መርሐ ግብርም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በመትከል የሀገራችን የደን ሽፋን ማሳደግ ችሏል። ይህም የአካባቢ ጥበቃን ከማረጋገጥ ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የግብርና ምርታማነትን በመጨመር የዜጎችን የረጅም ጊዜ የዕለት ተዕለት ሕይወት ዋስትና የሚያረጋግጥ ነው።

ማንኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ሊለካ የሚገባው በሚያቀርበው ፍልስፍና ብቻ ሳይሆን ለዜጎች በሚያጎናጽፈው ሁለንተናዊ ብልጽግና፣ በተለይም በሚጨምረው ምርት እና በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በመሠረተ ልማት ዘርፍ በሚያመጣው ለውጥ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተገለጸው ይህ መርህ የመደመር መንግሥት አካሄድም ሆነ የፖለቲካ ውሳኔዎች ሁልጊዜም ቢሆን የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ማሻሻልን ማዕከል ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው።

የመደመር መንግሥት የሚያከናውናቸው መዋቅራዊና ማኅበራዊ ፕሮጀክቶችም ይህንኑ እውነት በመሬት ላይ እያረጋገጡ ይገኛሉ።

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: