Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ ያደረጉት ንግግር ዋና ዋና ሐሳቦች

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 89

• የማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ እና የመንግሥት ውሳኔ ትክክለኛ መለኪያ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት ማሻሻል መቻሉ ነው።

• ዕድገት እና ለውጥ ወደ ዜጎች ደጃፍ ካልደረሰ፣ ሕዝቡ በፓርቲዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ እምነት ያጣል።

• ብልጽግና ፓርቲ 17 ሚሊዮን አባላት ያሉት አንድ ሀገራዊ ፓርቲ በማምጣት፣ ከመሪ እስከ አባላት በሕግ እና በውጤት የሚመዘኑበትን ሥርዓት ዘርግቷል።

• የሐሳብ ልዩነት ቢኖርም ለሀገር በጋራ መሥራት እንደሚገባ፤ ለዚህም በምርጫ ወቅት በሕግ አውጪው አካል ከሚገኙት የፓርላማ መቀመጫዎች 15 በመቶውን ለተፎካካሪዎች መተውና የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ ማካተት ተችሏል።

• የግሉ ዘርፍ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር የቴሌኮም እና የባንክ ዘርፎችን ለውድድር እና ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ፣ እንዲሁም በገበያ የሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ተመን ተግባራዊ ተደርጓል።

• ከ53 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ‘ፋይዳ’ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ እንዲይዙ በማድረግ፣ ዜጎች የባንክ እና የትምህርት አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ተደርጓል።

• ቀደም ሲል ተጀምረው የተጓተቱ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ የመደመር አካል በመሆኑ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለኢትዮጵያ እና ለጎረቤት ሀገራት ኃይል እንዲያቀርብ ተደርጓል።

• ለቀጣዩ ትውልድ ለም መሬት ለማስተላለፍ እና የአየር ንብረት አደጋዎችን (ድርቅና ጎርፍ) ለመቋቋም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

• መንግሥት ቢቀያየርም የማይቋረጡ የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ዕቅዶች ላይ ገዢ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች መስማማት እንዳለባቸው (ተፎካካሪዎች አፈጻጸሙን እየሞገቱ ግቡን መደገፍ ይችላሉ) ተመላክቷል።

• የሀገራት የዕድገት ግስጋሴ እንዳይቋረጥ ለወጣቶች እውነተኛ ኃላፊነት መስጠት እንደሚገባ እና ለዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ አመራር ልሕቀት አካዳሚን ለሁሉም የአፍሪካ ፓርቲዎች ክፍት ማድረጓ ተገልጿል።

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: