ገዢ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖሊሲ ልዩነቶች ሳይገድቧቸው በጋራ ግብ ላይ መስማማትና አዲስ መሪዎችን ማፍራት ይገባቸዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፣ ከምርጫ በላይ የሆኑ እና የሀገርን የረጅም ጊዜ የልማት ግቦች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊያስቀጥሉ የሚችሉ የብሔራዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
የፖሊሲ ልዩነቶች ቢኖሩም ገዢ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዋና ዋና የረጅም ጊዜ ግቦች ላይ ሊስማሙ እንደሚገባ በማሳሰብ፣ "ፖሊሲዎቻችን ይለያያሉ፣ መራጮች ይመርጣሉ፣ ነገር ግን አንዳንድ ብሔራዊ ጥረቶች ለመንግሥት ውጥን መትረፍ አለባቸው" ሲሉ አስረድተዋል።
በተጨማሪም አዲስ መሪዎችን ማፍራት እና ተተኪዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ጠንካራ መሪዎች ተተኪዎችን ሳያዘጋጁ ሲቀሩ በሀገራት ጉዞ ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በማስታወስ፤ ለሌሎች አባላት ተጨማሪ ኃላፊነት መስጠት እና ፍርድንና ታማኝነትን የሚያሳዩትን ማስተዋወቅ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመሪዎች የልህቀት አካዳሚ (African Leadership Excellence Academy) በኩል ሥልጠናውን ለአህጉሪቱ ፓርቲዎች ሁሉ ክፍት በማድረግ የበኩሏን አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን ገልጸዋል።
የምርጫ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የትምህርት እና የልማት ጉዞው ተቋርጦ እንደማይቀጥል አጽንኦት ሰጥተው፣ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ከፍታ በመመኘት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: