Search

ከአፍሪካ ሕብረት እስከ ኮፕ 32፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ የምታስመዘግበው ታሪካዊ ምዕራፍ

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 107

መዲናችን አዲስ አበባ ለዓመታት የአፍሪካ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ የልብ ትርታ ሆና የቆየች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች እና ተመራማሪዎች ተሰብስበው የአህጉሪቱን የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑባት፣ የሚደራደሩባት እና የጋራ ራዕይ የሚቀርጹባት ናት።

ከተማዋ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) ዋና መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ ከ130 በላይ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆኗ ከኒው ዮርክ እና ጄኔቫ ቀጥሎ በዓለም ላይ ሦስተኛ የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት።

በየዓመቱ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ ልምዷም አዲስ አበባን የሐሳብ መፍለቂያ፣ የአጋርነት መሠረት እና የተጨባጭ ተግባራት መነሻ አድርጓታል።

ይህ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ጥንካሬ፣ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ውስጥ እያገኘች የመጣችውን መሪ ስፍራ በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል።

በቅርቡ በከተማዋ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የተቀረጸው እና የጋራ አህጉራዊ አቋምን ያንጸባረቀው ታሪካዊው “የአዲስ አበባ ስምምነት እና የትግበራ ጥሪ” የአፍሪካን ወጥ ድምፅ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያበሰረ ነበር።

ኢትዮጵያ ይህንኑ የአፍሪካ የአየር ንብረት መፍትሔ፣ የፋይናንስ ፍትህ እና የታዳሽ ኃይል ልማት አጀንዳ በጽናት በመያዝ፣ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በከፍተኛ ዝግጅት ለማስተናገድ እየተሸጋገረች ትገኛለች።

ይህን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ማስተናገድ ሀገራችን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል፣ የተበላሹ መሬቶችን በማንሰራራት እና በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ያስመዘገበችውን በተግባር የተደገፈ ውጤት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽ የምታሳይበት ታላቅ የፖሊሲና የእውቀት መድረክ ነው።

የዓለም መሪዎችን፣ የፖሊሲ አውጪዎችን፣ ሳይንቲስቶችን እና የአካባቢ ተሟጋቾችን በአዲስ አበባ በሚሰበስበው በዚህ ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚበጁ አህጉራዊ መፍትሔዎችን በግንባር ቀደምትነት የምታመላክት ይሆናል።

COP32 ለሀገራችን የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም በሮችን በሰፊው የሚከፍት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ እንግዶች ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ወቅት የሀገራችንን መልካም ገጽታ እና የቱሪዝም መስህቦች ከመገንባት ባለፈ፣ የሆቴል፣ የትራንስፖርት፣ የንግድ እና የአገልግሎት ዘርፎችን በከፍተኛ ሁኔታ በማነቃቃት ለሀገራዊ ኢኮኖሚው ትልቅ ለውጥ ይዞ ይመጣል።

ይህ ታላቅ ኩነት ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ የምትገነባውን አረንጓዴ፣ ጽኑ እና የበለጸገች ሀገር ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያረጋግጥ ሌላው የወርቅ ምዕራፍ ይሆናል።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: