Search

“የምንከተለው ፖሊሲ ‘የሕዝባችንን የዕለት ተዕለት ሕይወት ቀይሯል ወይ?’ የሚለው ጥያቄ ዋነኛ የሕልውና መለኪያ ነው”፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 148

"የሕዝባችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በምንከተለው ፖሊሲ እና እምነት ምክንያት የተሻለ ሆኗል ወይ?” የሚለው ጥያቄ እያንዳንዱ የፖለቲካ መሪ ራሱን ሊጠይቅ የሚገባው ዋነኛ የሕልውና መለኪያ መሆን እንደሚገባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።

“ለዕድገት መምራት፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መፃኢ የኢኮኖሚ መሐንዲሶች” በሚል መሪ ሐሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ባለው ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመክፈቻ ንግግር አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው፣ አንድ ወላጅ ልጅን ወደ ትምህርት ቤት ሲወስድድ ሀገሩ ለልጁ የተሻለ ነገን እንደምትገነባለት ባለው ትልቅ ተስፋ እንደሆነ ገልጸው፣ ዕድገት እና ልማት ወደ ሕዝቡ ደጃፍ ካልደረሰ ግን ሕዝቡ በፓርቲዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንደሚያጣ አስጠንቅቀዋል።

ይህንን አህጉራዊ ፈተና ለመሻገር ኢትዮጵያ የብልጽግና ፓርቲ የመሪነት መርሕ የሆነውን ‘መደመር’ ፍልስፍና እንደ መፍትሔ ተቀምጣለች። መደመር ልዩ ልዩ ሀገራዊ አቅሞችን ለጋራ ዓላማ ማስተባበር መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለያዩ ክልላዊ መሠረቶች ላይ የተመሠረቱ ድርጅቶችን ወደ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ በማቀናጀት ከ17 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት እና በውጤታማነት ራሱን የሚገመግም ግዙፍ ፓርቲ መገንባት መቻሉን አብራርተዋል።

የፖለቲካ አካታችነትን እና ዴሞክራሲያዊ ብስለትን በተመለከተም ኢትዮጵያ ታሪካዊ እርምጃ መውሰዷን በማንሣት፣ በምርጫ ወቅት ብልጽግና ፓርቲ በሕግ አውጪው አካል 15 በመቶ ከሚሆኑት መቀመጫዎች ላይ ዕጩ ባለማቅረብ እና ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር የተካተተበት የመደመር መንግሥት በማቋቋም በፖለቲካ ፉክክር እና በሀገራዊ አደራ መካከል ያለውን ሚዛን ማስጠበቁን አብራርተዋል።

የፖለቲካ ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው ሀገራዊ ተቋማትን በጋራ መገንባት የመደመር አስተሳሰብ እውነተኛ መገለጫ መሆኑንም አክለዋል።

የምርጫ ውጤት ምንም ይሁን ምን አንድ ወላጅ ልጁን ወደ ትምህርት ቤት የመውሰድ ተስፋ እና ሀገራዊ ጉዞ የማይቆም በመሆኑ፣ አፍሪካውያን መሪዎች የሚያምኑበትን የፖለቲካ እሳቤ በዜጎች የሕይወት መሻሻል እና በተግባራዊ ውጤት ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስምረውበታል።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: