Search

የአፍሪካ መጻኢ ዕድል የተመሠረተው ሀገራዊ አቅማችንን ወደ ውጤታማ አቅም መቀየር በምንችልበት ቁመና ላይ ነው፦ አቶ አደም ፋራህ

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 171

በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የአፍሪካ የኢኮኖሚ መጻኢ ዕድል ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው የያዝነውን ሀገራዊ አቅም ወደ እውነተኛ እና ውጤታማ አቅም መቀየር በሚቻልበት ቁመና ላይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

“ለዕድገት መምራት፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ የኢኮኖሚ መሐንዲሶች” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ አደም ፋራህ፣ የፖለቲካ ኃላፊነት ሁልጊዜም የልማት እና የዕድገት ማዕከል ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ይህንን ታሪካዊ ሀገራዊ ኃላፊነት እየተወጣ የሚገኘው የፓርቲው ፕሬዚዳንት በሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተቀረጸው የመደመር ሀገር በቀል ፍልስፍና ላይ በመመሥረት መሆኑን ጠቁመው፣ መደመር ሰዎችን፣ ተቋማትን እና ስኬቶችን በጋራ ዓላማ ዙሪያ በማሰባሰብ መከፋፈልን የሚያሸንፍ እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚገነባ የለውጥ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርቲው የሰብአዊ ክብርን፣ ፀጥታን፣ የኢኮኖሚ ዕድልን እና ማኅበራዊ ደኅንነትን የሚያረጋግጥ ውጤታማ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጥብቅ ቁርጠኝነት እንዳለው ያነሡት አቶ አደም ፋራህ፣ ዛሬ ላይ ፓርቲው ወደ 17 ሚሊዮን አባላት እና ጠንካራ ሀገር አቀፍ መዋቅሮች ያሉት መሆኑን አስታውሰዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላም እና ለልማት ግልጽ አቅጣጫ ሊሰጡ፣ ኢንቨስትመንትን ማሰባሰብ፣ አዳዲስ ክህሎቶችን ማዳበር እና በትውልዶች መካከል ያለውን ዕድገት የሚያስቀጥሉ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አካታች ፖለቲካን እውን ለማድረግም ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተውጣጡ ከ275 በላይ መሪዎችን በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ላይ በመመደብ የጋራ ሀገራዊ አደራ ማጠናከር መቻሉን ገልጸዋል።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: