ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ሕዝብ ጤና ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአህጉሪቱን የሕብረተሰብ ጤና ለመጠበቅ የሚያግዙ ሦስት ቁልፍ የመፍትሄ ሐሳቦች ላይ መግባባት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቧቸው ሦስት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል በርካታ ዜጎች ልዩ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት እንደሚጓዙና አገልግሎቱን ከቤታቸው በቅርብ ርቀት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የጤና ሥርዓቶች ጥራታቸውን የጠበቁ የአፍሪካ መድኃኒቶችን እና የጤና ምርቶችን በጋራ በመግዛት አስተማማኝ ገበያ መፍጠር እንደሚችሉ ገልጸው፣ ይህም አምራቾች ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ ምርታቸውን እንዲያስፋፉ እና በላቀ መተማመን እንዲያቀርቡ ያግዛል ብለዋል።
ለእያንዳንዱ ቃል ኪዳን ተጠያቂው ማን እንደሆነ፣ የገንዘብ ድጋፉ እንዴት እንደሚሸፈን እና አፈጻጸሙ መቼ እንደሚገመገም ግልጽ ማድረግ እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ስኬት ሕዝቡ በሚያገኘው ሕክምና ላይ በሚያየው ተጨባጭ መሻሻል መለካት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ኅብረት በአህጉሪቱ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን እና ዲጂታል ጤናን የማሳደግ ኃላፊነት እንደሰጣቸው ገልጸው፣ በኢትዮጵያ ይህንን አካሄድ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” እንደሚመራው አስታውቀዋል።
ዲጂታል ጤና የዕለት ተዕለት የሕክምና አገልግሎት አካል እንዲሆን የሚያስችሉ መሣሪያዎችን የሚነድፉና የሚፈትሹ አፍሪካውያን ተመራማሪዎች እና የጤና ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል። ይህም የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ቀጣይነት ያለው የገንዘብ ድጋፍ እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።
የጤና መረጃዎች አህጉሪቱ በምታወጣቸው ደንቦች እና እውቀትን ለማጋራት በሚዘረጉ አስተማማኝ አሠራሮች ሥር መጠበቅ እንዳለባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: