Search

ዲጂታል ጤና እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለአፍሪካ የዕለት ተዕለት ሕክምና መሠረት ሊሆኑ ይገባል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሰኞ ኅዳር 14, 2019 23

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ5ኛው የአፍሪካ ማኅበረሰብ ጤና ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የጤና ባለሙያዎች በሚሠሩበት ማንኛውም ስፍራ ሆነው ፈጣን እና አስተማማኝ የባለሙያ ምክር ማግኘት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሩቅ ወረዳ የሚገኝ አዋላጅ ችግር ሲያጋጥመው ከስፔሻሊስት ጋር እንዲመካከር እና የክልል ሆስፒታል ሐኪም ምስሎችን ለምርመራ እንዲልክ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የታካሚዎች የሕክምና መረጃ ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም በደኅንነት መተላለፍ መቻል እንዳለበት አመልክተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት በአኅጉሪቱ ሰው ሠራሽ አስተውሎትንና ዲጂታል ጤናን የማራመድ ኃላፊነት እንደሰጣቸው አስታውሰዋል፡፡

ቴክኖሎጂው በአካባቢያዊ ሁኔታዎች ተፈትሾ ሲረጋገጥ የጤና ባለሙያዎችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያም "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ይህንኑ አካሄድ እንደሚመራ ተናግረዋል።

ዲጂታል ጤና የዕለት ተዕለት የሕክምና አገልግሎት አካል እንዲሆን አፍሪካውያን ተመራማሪዎች እና የጤና ባለሙያዎች መሣሪያዎቹን ራሳቸው ቀርጸው ሊፈትሿቸው ይገባል ብለዋል።

ቴክኖሎጂዎቹም በአፍሪካ ቋንቋዎች እና ባለሙያዎቹ በሚገጥሟቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚሠሩ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ይህንን እውን ለማድረግም የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ቀጣይነት ያለው የገንዘብ ድጋፍ እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።

የጤና መረጃዎች በራሳችን ሕግና ደንብ መጠበቅ እንዳለባቸው እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የዕውቀት ልውውጥ በአስተማማኝ ሥርዓት መከናወን እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት ከአፍሪካ የጤና ተቋማት ጋር የጋራ ጥናት እና ምርምር ማካሄድ እንደሚችል ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው የመደመር ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲም የላቀ ሥልጠና እና ምርምር በማስፋት ከመላው አፍሪካ የሚመጡ ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ለታዳጊ ሳይንቲስቶች የምርምር ላቦራቶሪዎች፣ የገንዘብ ድጋፍ እና የሥራ ዕድሎች ሊመቻቹላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: