ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ተልዕኮን ለማሳካት እገዛ እንደሚያደርጋት የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
ኢትዮጵያ በካናዳ ሞንትሪያል በተካሄደው የዓለም-አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) 43ኛ ልዩ ጉባኤ የድርጅቱ ምክር ቤት አባል ሀገር ሆና መመረጧ ይታወሳል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንደ ሀገር በተደረገው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲሁም መንግሥት ለአቪዬሽን ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የሕግ ማዕቀፍ ከማሻሻል አንስቶ በተከናወኑ ሁለንተናዊ ሪፎርሞች በተከታታይ ዓመታት በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ በተመዘገቡ ተጨባጭ ስኬቶች ከብሔራዊ ተልዕኮ ባሻገር ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተገዢ የመሆን ዕይታን ማጎልበት መቻሉ ኢትዮጵያን ተመራጭ አድርጓታል ብሏል፡፡
ሀገራችን በዘርፉ የደረሰችበትን ዕድገት እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወዳዳሪነት ጋር የሚመጣጠን ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ተከትሎ የተገኘው የምክር ቤት አባልነት፣ ዕድል ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ደኅንነት የማረጋገጥ ተልዕኮውን ለማሳካት እገዛ እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡
የዓለም-አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) 43ኛው ልዩ ጉባኤ የምክር ቤት አባላትን ቁጥር ከ36 ወደ 40 ለማሳደግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የተካሄደ ሲሆን፣ የአፍሪካ ሕብረት ኢትዮጵያ የአህጉሪቱ ብቸኛ ዕጩ ሆና እንድትወከል ምክረ-ሐሳብ በማቅረቡና የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) አባል ሀገራትም ሙሉ ድጋፋቸውን በመስጠታቸው ለምክር ቤቱ አባልነት የተወዳደረችው ሀገራችን ከፍተኛ ድምጽ አግኝታ ተመርጣለች፡፡
ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል መሆኗ ከዚህ ቀደም በአባልነት ከነበራት ተሳትፎ በተጨማሪ በድርጅቱ አሠራሮች ላይ በተለይም የውሳኔ ሰጪነት ሚናዋን ከፍ በማድረግ በዘርፉ ዓለም-አቀፍ ተወዳዳሪ ተቋም ለመሆን የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1412/18 መሰረት የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደኅንነት ሥራዎችን በበላይነት የመምራት፣ የማስተባበርና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን አገልግሎቱ ባወጣው መረጃ አስታውሷል።
በፈረንጆቹ 2024 እንዲሁም በ2025 ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ባካሄደው ጥልቅ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲት ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የደኅንነት ስጋትና ክፍተት እንደሌለባት በማረጋገጥ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን በብቃት ማሟላቷን አረጋግጧል፡፡
በካናዳ ሞንትሪያል በተካሄደው የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) 42ኛ ጉባኤ እና በካዛኪስታን አስታና ከተማ በድርጅቱ አዘጋጅነት በተካሄደው የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ሳምንት ሲምፖዚየም ላይ ተሳትፎ በማድረግ ተቋማዊና ሀገራዊ ተሞክሮዋን ማጋራትም ተችሏል፡፡
በመሆኑም መንግሥት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ ሜጋ ፕሮጀክት ቀርፆ ዘርፉን ለማሳደግ በቁርጠኝነት የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ከዳር ለማድረስ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በጊዜ የለንም መንፈስ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚያስችል ተቋማዊ ቁመና እየገነባ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ምክር ቤት የድርጅቱ ቋሚ የአስተዳደር አካል ሲሆን የበረራ ደኅንነትን፣ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ስታንዳርዶችን፣ ተመራጭ ምክረ-ሐሳቦችን፣ የኦዲት ቁጥጥር ተግባራትን፣ የአየር አሰሳንና የአካባቢ ጥበቃን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችንና የሚመከሩ አሠራሮችን ያጸድቃል፣ ያሻሽላል፤ በአባል ሀገራት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችንም ይመለከታልም ነው ያለው አገልግሎቱ በመረጃው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: