ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የኩስመና ታሪክ ማብቂያ" በሚል ርዕስ ባደረጉት የጉባ ላይ ወግ ቆይታ፣ "ፈጣሪ ሲፈጥረን በነፃ፣ ሲሰጠን በነፃ፣ ሲፈቅድልን በነፃ ስለሆነ አመሰግናለሁ ከማለት በላይ ብዙ የሚባል ነገር የለም" ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተሠራበት ቦታን አስደናቂነት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም አንዳንዶች እንደሚሉት “ኢትዮጵያ ፈጣሪ እጁን ታጥቦ የሠራት ምድር ነች” ለሚለው ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
የመልክዓ ምድሩ አፈጣጠር አስደናቂነት በነፃ የተሰጠን ብዙ ነገር የሚታይበት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ግድቡ የተሠራበት ቦታ ያሉት ተራሮች ፈጣሪ ውኃውን ብቻ ሳይሆን ውኃውን የምናስቀርበት ተፈጥሮ እንደተሰጠን ማሳያ እንደሆነ አውስተዋል።
"ወርቅን ከሚንጎማለል ውኃ ጋር አጣምሮ የሰጠንን ፈጣሪ ከማመስገን በስተቀር ምን ማለት እንችላለን!" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ "እኛ ግን የተሰጠንን ማየት የተሳነን ሰዎች እንደሆንን ይሰማኛል" በማለት ፀጋዎቻችንን ባለመጠቀማችን ለችግር መጋለጣችንን ጠቁመዋል።
"በአፍሪካ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ በረሃብ የተጠቀሰ ሀገር እንደሌለ ሲታይ የተሰጠንን ፀጋ ባለመጠቀማችን የረሃብ ምሳሌ በመሆናችን ፈጣሪ እንደሚያዝንብን ይሰማኛል" በማለት ነው ስሜታቸውን የገለጹት።
ኢትዮጵያውያን በፈጣሪ መኖር የሚያምኑ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁሉም ስለተሰጠን ፀጋ አመስግኖ እና ተጠቅሞበት ከችግር ለመውጣት መትጋት አለበት ብለዋል።
በለሚ ታደሰ
#PMOEthiopia #AbiyAhmed #EBC #ebcdotstream #GERD #naturalgift