Search

የሆርሙዝ መዘጋት፣ የነዳጅ ገበያ መናወጥ እና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ስጋት

ረቡዕ መጋቢት 02, 2018 108

የካቲት 21 ቀን 2018 . በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥምረት በኢራን ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ መናወጥ እያስከተለ ይገኛል። 

ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ ባሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ቢያንስ 85 ሀገራት በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በማድረጋቸው ሸማቾች ለከፍተኛ ጫና ተዳርገዋል።

በአሜሪካ የአንድ ጋሎን ነዳጅ ዋጋ 20 በመቶ በማደግ በአማካይ 3.58 ዶላር የደረሰ ሲሆን፥ እንደ ካሊፎርኒያ ባሉ ግዛቶች ደግሞ ዋጋው 5 ዶላር በላይ በመሻገር ላለፉት ሁለት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ይህ የዋጋ ንረት በእስያ ሀገራት ላይ ይበልጥ የከፋ ሆኖ ተመዝግቧል፤ ለምሳሌ ቬየትናም 50 በመቶ፣ ላኦስ 33 በመቶ እንዲሁም ካምቦዲያ እና አውስትራሊያ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ካደረጉ ሀገራት ተርታ ተሰልፈዋል።

ለእስያ ሀገራት የነዳጅ ዋጋ መናር ዋነኛው ምክንያት ለኃይል ፍጆታቸው በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ ያላቸው ከፍተኛ ጥገኝነት ነው። የባሕር ወሽመጡ በጦርነቱ ሳቢያ በመዘጋቱ ምክንያት እንደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሀገራት የኃይል ገበያቸውን ለማረጋጋት አስቸኳይ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረዋል።

ጃፓን እና ፈረንሳይ የስትራቴጂክ የነዳጅ ክምችታቸውን ለመልቀቅ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን፣ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ላለፉት 30 ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ በነዳጅ ዋጋ ላይ የጣሪያ ገደብ ጥላለች።

በሌላ በኩል እንደ ፓኪስታን እና ባንግላዴሽ ያሉ አነስተኛ የፋይናንስ አቅም ያላቸው ሀገራት የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ ሲሉ የትምህርት ቤቶችን መዘጋት እና ከቤት ሆኖ የመሥራት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ።

የቡድን ሰባት (G7) ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮችም ይህንኑ ዓለም አቀፍ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል።

የነዳጅ ዋጋ መናር ከማደያዎች ባለፈ በዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና እና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ጥላውን አሳርፏል። የነዳጅ ዋጋ እና የምግብ ዋጋ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው፣ ከማዳበሪያ ምርት ጀምሮ ምርቶችን ወደ ገበያ ለማጓጓዝ የሚያስፈልገው ከፍተኛ ወጪ ለምግብ ዋጋ ንረት ዋነኛ መንስኤ ሆኗል።

ፕላስቲኮች፣ ሰው ሠራሽ ጨርቃጨርቆች እና መዋቢያዎችም ከነዳጅ ተዋጽኦ የሚመረቱ በመሆናቸው የዋጋ ጭማሪው በሁሉም የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ሰፊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረባቸው የቀድሞ ዓመታት ሁሉ የዓለም የኢኮኖሚ ድቀት መከሰቱን በማስታወስ፣ አሁንም እንደስታግፍሌሽንያሉ ቀውሶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ያለውን የጂኦ-ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ወደ ሁለንተናዊ የኑሮ ቀውስ እየቀየረው እንደሚገኝ የአልጄዚራ ትንታኔ ያመላክታል።

ለሚ ታደሰ