Search

የአዲሲቷ አዲስ አበባ ግርማ ሞገስ በካሜሩናዊው ጎብኚ አንደበት፦ "የአፍሪካ የውበትና የብልፅግና ተምሳሌት

ሓሙስ መጋቢት 03, 2018 51

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ፣ በቅርብ ዓመታት እያስመዘገበችው ባለው ፈጣንና አጠቃላይ የከተማ ልማት የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ቀልብ መሳቧን ቀጥላለች።

ከተማዋ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በዘመናዊ መሠረተ ልማትና ውበት በማጀብ "የአፍሪካ እምብርት" ለሚለው ስሟ አዲስ ትርጉም እየሰጠችው ትገኛለች። ሰሞኑን ከተማዋን የጎበኙ የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜጎች እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ ንፅህናዋ የተጠበቀ፣ ሰፊና ዘመናዊ መንገዶች ያሏት እንዲሁም በሥነ-ሕንጻ ጥበብ የተዋቡ ሕንጻዎች የሚታዩባት ማራኪ ከተማ ሆናለች።

ይህንን የአዲስ አበባን አዲስ ገጽታና የልማት ጉዞ ለዓለም ካጋሩ የውጭ ዜጎች መካከል ካሜሩናዊው ታዋቂ ብሎገር አቴም ሃሪስ አንዱ ነው። ሃሪስ በአዲስ አበባ በቆየባቸው ቀናት የዓድዋ ድል መታሰቢያን፣ የአፍሪካ ሕብረት አዳራሽንና ዘመናዊ የከተማዋን ጎዳናዎች ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

በተለይ ወዳጅነት ፓርክን በጎበኘበት ወቅት በታየው ለውጥ እጅግ በመደመም "ይህ የኢትዮጵያ እውነተኛ ውበት ነው" ሲል ስሜቱን ገልጿል።

ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያ የነበሩ ስፍራዎች ዛሬ ወደ ውብ መዝናኛነት መቀየራቸው የከተማዋን ነዋሪዎችና ጎብኚዎችን በእጅጉ ያስገረመ ሲሆን፣ ምሽት ላይ የሚታየው የውኃና የብርሃን ትዕይንት ደግሞ ለከተማዋ ልዩ ድባብን ሰጥቷታል።

የከተማዋ ደኅንነትና የነዋሪዎቿ እንግዳ ተቀባይነት ለጎብኚዎች ትልቅ መተማመኛ ሆኖ ተመዝግቧል። አዲስ አበባ በማንኛውም ሰው በዘርና በቀለም ልዩነት ሳይገደብ ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድና የሁሉንም ልብ የምትገዛ ከተማ ሆናለች።

እንደ ወዳጅነት ፓርክ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ወደፊት እያደረገች ያለውን የልማት ጉዞና የአረንጓዴ ልማት ስራ የሚያሳዩ ትልቅ ተምሳሌቶች መሆናቸውን የገለጸው አቴም ሃሪስ አዲስ አበባ ዛሬም ነገም የአፍሪካ የውበት፣ የሰላምና የዘመናዊነት ማሳያ ሆና ትቀጥላለች።

በላሉ ኢታላ

 

#AddisAbaba #Ethiopia #TourismEthiopia #FriendshipPark #AdwaMemorial #AfricaRising #አዲስአበባ #ኢትዮጵያ #ልማት #ቱሪዝም