የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን (ተመድ) ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በአውሮፓ ተወካይነት የመሩት ፖርቹጋላዊው አንቶኒዮ ጉተሬዥ፣ በአውሮፓውያኑ 2026 የሥልጣን ዘመናቸውን ያጠናቅቃሉ።
ይህንን ተከትሎም የዓለምን ቁንጮ ዲፕሎማሲያዊ መንበር ለመያዝ የሚደረገው የፉክክር ምዕራፍ በይፋ መጀመሩን ድርጅቱ አስታውቋል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ ምርጫ ሂደት በድርጅቱ ቻርተር አንቀጽ 97 መሠረት አራት ዋና ዋና ሂደቶችን ማለፍ ይኖርበታል። ሂደቱ የሚጀምረው በጠቅላላ ጉባኤውና በጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንቶች ጥሪ አማካኝነት አባል አገራት ብቃት ያላቸውን እጩዎች ሲጠቁሙ ነው።

እጩዎቹ የሕይወት ታሪካቸውንና ድርጅቱን እንዴት ለመምራት እንዳቀዱ የሚያሳይ "የራዕይ መግለጫ" (Vision Statement) ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ምንም እንኳ በቅርብ ዓመታት ሂደቱ ግልጽነት እንዲኖረው እጩዎች በጠቅላላ ጉባኤው ፊት ቀርበው "የሥራ ቃለ-መጠይቅ" መሰል መድረክ ቢዘጋጅላቸውም፣ የመጨረሻው ውሳኔ ግን በጸጥታው ምክር ቤት 15 አባላት እጅ ላይ ይወድቃል።

በተለይም አምስቱ ቋሚ አባላት (አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ) ማንኛውንም እጩ ድምጽን በድምጽ የመሻር "ቬቶ" የመቃወም ፍጹም ሥልጣን አላቸው።
ድርጅቱ ከተመሠረተ 80 ዓመታት ቢቆጠሩም፣ እስካሁን ዘጠኙም ዋና ፀሃፊዎች ወንዶች ናቸው። አሁን ግን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ድርጅቱን በሴት መሪ ለማስመራት የሚደረገው ዓለም አቀፍ ግፊት ከፍ ብሏል። እስካሁን የቀረቡት እጩዎችም ይህንን ግፊት ያንፀባርቃሉ።

የቀድሞዋ የቺሊ ፕሬዚዳንት ቬሮኒካ ባቼሌት ጄሪያ፣ የቀድሞዋ የኮስታሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪቤካ ግራይንስፓን እና አርጀንቲናዊው የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ተቆጣጣሪ ተቋም (IAEA) ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ በዋናነት የሚጠቀሱ እጩዎች ናቸው።
አፍሪካ ቀደም ሲል በግብፃዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ እና በጋናዊው ኮፊ አናን አማካኝነት ድርጅቱን መርታለች። በዘንድሮው ፉክክር ብሩንዲ የቀድሞውን የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳልን አፍሪካን ወክለው እንዲመረጡ በእጩነት አቅርባለች።
ምንም እንኳ የቦታው ክፍተት በአህጉራት መካከል በየተራ የመዞር "ያልተጻፈ ሕግ" ቢኖርም፣ የአፍሪካ ዳግም መመረጥ ወይም የላቲን አሜሪካ እጩዎች ዕድል በኃያላኑ ሀገራት ስምምነት ላይ የተመሰረተ ይሆናል።
የዘንድሮው ምርጫ የተመድ መሪነትን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያሸጋግራል ተብሎ በትልቅ ጉጉት ይጠበቃል።
በላሉ ኢታላ