Search

14ኛ ቀኑን የያዘው የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ወደ ዓለም አቀፍ ቀውስ ያመራል የሚል ስጋት ደቅኗል

ዓርብ መጋቢት 04, 2018 135

በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ግጭት 14ኛ ቀኑን ሲይዝ፣ ከቀጣናዊ ስጋትነት አልፎ ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ኢኮኖሚ ከፍተኛ ፈተና መሆኑን ቀጥሏል።

አሜሪካ እና እስራኤል በጥምረት ከኢራን ጋር እያደረጉ ያለው ጦርነት፣ አሁን ላይ በበርካታ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት እያስከተለ ይገኛል።

በወታደራዊ መስኩ የአሜሪካ ኬሲ-135 (KC-135) ነዳጅ ጫኝ አውሮፕላን በኢራቅ መከስከስ እና የፈረንሳይ ከፍተኛ መኮንን መገደል፣ ግጭቱ የዓለምን ኃያላን በቀጥታ እያሳተፈ መሆኑን ማሳያ ሆኗል።

በሊባኖስ በኩል ከ634 በላይ ሰዎች መገደላቸው እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸው ደግሞ የሰብአዊ ቀውሱን አሳሳቢነት አጉልቶታል። 

ከጦርነቱ ጎን ለጎን በኢራን 190 ከተሞች የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ መንግሥት ኢንተርኔት እንዲዘጋ አስገድዷል።

አዲሱ የኢራን የበላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ ተዘግቶ እንደሚቀጥል መግለጻቸው፣ የዓለምን የነዳጅ አቅርቦት አንድ አምስተኛ በማስተጓጎል የአንድ በርሜል ዋጋ ከ100 ዶላር በላይ እንዲያሻቅብ አድርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ግጭቱ መቋጫ እንዲያገኝ የውሳኔ ሐሳብ ቢያቀርብም፣ በአሜሪካ እና ኢራን መሪዎች መካከል ያለው ፍጹም የአቋም መካረር ለሰላም የሚደረገውን ጥረት አዳጋች አድርጎታል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁኔታው ወደ ከፋ ቀጣናዊ ጦርነት እንዳያመራ እና የዓለምን ደኅንነት እንዳያናጋ፣ አሁኑኑ የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅበት ተንታኞችን ጠቅሰው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን እየዘገቡት ይገኛል።

ለሚ ታደሰ 

#MiddleEastCrisis # #HormuzStrait #UNSecurityCouncil