Search

ኢትዮጵያ ከምድር በታች የታቀፈችው የማዕድን በረከት

ሓሙስ መጋቢት 03, 2018 74

ኢትዮጵያ ስሟ ሲነሳ የጥንታዊ ሥልጣኔና የባህል ማማ ሆና መታየቷ የታወቀ ነው። ሆኖም ከታሪካዊ ስሟ ባሻገር፣ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረትን እየሳበች ያለችው ከእግራችን በታች ባለው "የማዕድናት ግምጃ ቤት" በሚያስብላት ተፈጥሯዊ ጸጋዋ ነው።
እነዚህ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ ከመሆናቸውም በላይ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መጠናከር ወሳኝ ሚና አላቸው።
በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ወርቅ የውጭ ምንዛሬ ዋነኛ ምንጭ በመሆን ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል። በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይና ጋምቤላ ክልሎች በስፋት የሚገኘው ይህ ውድ ሀብት፣ የሀገሪቱን የፋይናንስ አቅም ከፍ የሚያደርግ ታላቅ በረከት ነው።
ከዚህም ባለፈ እንደ ኦፓል፣ ኤመራልድና ሳፋየር ያሉ ማራኪ የከበሩ ድንጋዮች እንዲሁም ለረቂቅ ቴክኖሎጂዎች ግብዓት የሚውለው ፕላቲኒየም የኢትዮጵያ ምድር የታደለች መሆኗን ማሳያ ናቸው።
ዓለማችን ወደ አረንጓዴ ኢነርጂ በምትሻገርበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የወደፊቱ ተስፋ ባለቤት ሆና ብቅ ብላለች። ለኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎች ወሳኝ የሆነው ሊትየም እና ለከፍተኛ የኢንዱስትሪ ሥራዎች የሚውለው ታንታለም በምድራችን የታቀፉ የሀብት ምንጮች ናቸው።
በአፋር ዳሎል የሚገኘው ፖታሽ ደግሞ ለግብርና ማዳበሪያ ምርት የሚውል ስትራቴጂካዊ በረከታችን ነው።
በተጨማሪም ለግንባታና ለኃይል አቅርቦት የሚውሉ እንደ የድንጋይ ከሰል፣ ብረትና የኖራ ድንጋይ ያሉ ማዕድናት የሀገር በቀል ኢኮኖሚውን በጽኑ መሠረት ላይ እየገነቡ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘርፉን ከጥቁር ገበያ ተጽዕኖ በማውጣት ወደ ይፋዊ የኢኮኖሚ መዋቅር እንዲገባ አስችሎታል። ይህም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በዘላቂነት ለመቅረፍና የማዕድን ዘርፉ ተጨባጭና ፈጣን ለውጥ እንዲያስመዘግብ ትልቅ ፋይዳ አበርክቷል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ