Search

የጥንቱ ድንቅ የታሪክ ሙዚየም፣ የዛሬው የሚያብብ የምስራቅ ዕንቁ

ቅዳሜ መጋቢት 05, 2018 50

የዘመናት አሻራ የታተመባት፣ እንደ ውድ ዕንቁ የምታበራው የታሪክ መናገሻ ሐረር፤ ዛሬም የታሪክ መዳረሻና የጥበብ ምንጭ ሆና ቀጥላለች።
ሐረርን መጎብኘት ታሪክን በዓይነ-ሕሊና መሳል ሳይሆን፣ በሺህ ዓመታት የታጠረችውን ሕያው ሙዚየም በእጅ የመንካት ያህል የሚቆጠር ጥልቅ ተሞክሮ ነው።
ይህች ከተማ የፈላስፎች፣ የባለቅኔዎችና የነጋዴዎች የጋራ መድረክ ስትሆን፤ ፈረንሳዊው ገጣሚ አርተር ራምቦ የመሰከረላት ውበቷና የአሚሮች መናገሻነቷ ዛሬም በጠባብ መተላለፊያዎቿ ውስጥ የጥንቱን መዓዛና የሰላም ድባብ አቅፎ ይገኛል።
በጀጎል ግንብ ውስጥ የሚገኘው የሺህ ዓመታት አሻራ እና ከግንቡ ውጪ ያለው የዘመናዊነት ሩጫ ተደጋግፈውና ተስማምተው የሚጓዙበት ጥበብ እጅግ ያስደንቃል።
መስጊዶችና አብያተ ክርስቲያናት በመከባበር ቆመው፣ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ በፍቅርና በጉርብትና የሚኖሩባት እውነተኛዋ “የፍቅር ከተማ” ናት።
ከሀገረሰቡ የሐረሪ ቤት ጥልቅ መስተንግዶና ከታዋቂው የሐረር ቡና መዓዛ ጀምሮ፣ ማታ ማታ በተፈጥሮና በሰው መካከል ያለውን እንግዳ ትስስር እስከሚያሳየው የጅብ መመገብ ሥነ-ሥርዓት ድረስ ሐረር ተኖሮባት የማትጠገብ መዳረሻ ናት።
በአሁኑ ወቅት ሐረር ጥንታዊ ማንነቷን ከዘመናዊ የከተማ ልማት ጋር ለማጣጣም በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች። በተለይም በቅርቡ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከነበረባት “ጠባብና የተጨናነቀ” ገጽታ አውጥቶ፣ ሰፊ፣ ንጹሕና ማራኪ ወደሆነ የቱሪስት መዳረሻነት እየቀየራት ይገኛል።
ይህም የዓለም ቅርስነቷን በጠበቀ መልኩ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ትኩረት የተሰጠው ትልቅ የልማት እንቅስቃሴ ነው።
ሐረርን መጎብኘት ማለት በጊዜ ውስጥ ተጉዞ የወደፊቱን የሰላምና የውበት ዓለም እንደማየት ይቆጠራል።
በንፋታሌም እንግዳወርቅ