የሲዳማ ሕዝብ የዘመን መለወጫ "ፊቼ ጫምባላላ" በዓል የሚከበርበት ቀን በየዓመቱ ቋሚ አለመሆኑ፣ የብሔሩን የረቀቀ የቀን መቁጠሪያና የሥነ-ከዋክብት (አስትሮኖሚ) ጥበብ በግልጽ የሚያሳይ ክስተት ተደርጎ ይወሰዳል።
"አያንቶ" በመባል የሚታወቁት የሀገር ሽማግሌዎችና የሥነ-ፈለክ ጠቢባን የጨረቃንና የከዋክብትን እንቅስቃሴ በጥልቀት በመመርመር፣ አዲሱ ዓመት የሚባባርበትን ዕለት ይወስናሉ።
ይህ ጥንታዊ ሳይንሳዊ ስሌት፣ የሲዳማ ሕዝብ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ጥልቅ ቁርኝት የሚመሰክር ድንቅ ሀገራዊ እሴት ነው።

በዓሉ ከዘመን መለወጫነት ባለፈ፣ በሕዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምን የሚሰብክ ባህላዊ ሥርዓት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
የሲዳማ ሕዝብ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲስ ዓመት በሚሸጋገርበት ወቅት የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ለፈጣሪ የምስጋናና የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚቀርብበት ወቅት ነው።
ይህ ማኅበራዊ ትስስርን የማጠናከር ሚናው፣ በ2008 ዓ.ም በዩኔስኮ (UNESCO) በማይዳሰስ የሰው ልጅ ቅርስነት ለመመዝገብ አስችሎታል።

በፊቼ ጫምባላላ ሥነ-ሥርዓት ላይ የወጣቶችና የልጆች ድርሻም እጅግ የጎላ ነው። ወጣቶች ከቤት ቤት እየዞሩ የምስራች ሲያበስሩ፣ ሽማግሌዎች ደግሞ መጪው ዘመን የጥጋብና የሰላም እንዲሆን ምርቃት ይሰጣሉ።
ይህ ትውፊታዊ ሽግግር ባህሉ ሳይበረዝ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ከማድረጉም በላይ፣ በታላላቆችና በታናናሾች መካከል ያለውን መከባበር በተግባር የሚያሳይ ነው።
በበዓሉ ወቅት የሚቀርቡት እንደ "ቡሪሳሜና ጩካሜ" ያሉ ባህላዊ ምግቦችና በጋራ የመመገብ ሥርዓት፣ የብሔሩን የእንግዳ ተቀባይነትና የልግስና እሴት በጉልህ ያንጸባርቃሉ።
ፊቼ ጫምባላላ የብሔሩ ማንነት ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገትና ለብሔራዊ መግባባት ትልቅ አቅም ያለው የዓለም ቅርስ ሆኗል።
በዛሬው ዕለት የዘመን መለወጫ ዋዜማ የሆነው የ"ፊቼ" (ፊጣራ) በዓል በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች በውቢቷና በኮሪደር ልማት እንደ አዲስ በተሞሸረችው ሀዋሳ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የአዲስ ዓመት በዓል የሆነው "የጫምባላላ" በዓልም በነገው ዕለት በሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ በሚገኘው "ሶሬሳ ጉዱማሌ" አደባባይ፣ ባህላዊ እሴቱንና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።
በዮሐንስ አበረ