Search

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይልን ወደ ኢነርጂ አማራጮቿ ለማስገባት ከጣሊያን ጋር መከረች

ሓሙስ መጋቢት 03, 2018 60

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን (ENEC) እና ጣሊያን በዘርፉ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ ውይይት በአዲስ አበባ አካሂደዋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የኒውክሌር ኢነርጂን በሀገሪቱ የኃይል አማራጮች ውስጥ ማካተት ያለውን ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
በተለይም የኒውክሌር ኃይል አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በመስጠት ከፍተኛ ኃይል ለሚጠይቁ ኢንዱስትሪዎች እና ለሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል።
አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ በበኩላቸው ጣሊያን በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ምርምር እና ልማት ያላትን የካበተ ታሪክና ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ጣሊያን ዘርፉን ዳግም ወደ ኢነርጂ አማራጮቿ ለማስገባት እያጠናች ያለችበት ወቅት መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ ይህ የሁለቱ ሀገራት ፍላጎት ለጋራ ተጠቃሚነት ጠንካራ መሠረት እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ለሰላማዊ ዓላማ አጠቃቀም እያደረገች ያለችውን ጥረት ይበልጥ እንደሚያግዘውም ታምኖበታል።
በሃይማኖት ከበደ