Search

ለኪነ-ጥበብ ቤተሰቦች ተጨማሪ ብስራት የሆነውን እጅግ ዘመናዊ አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ማክሰኞ ጥቅምት 04, 2018 49

ዛሬ ለኪነ-ጥበብ ቤተሰቦች እና ለከያኒያን ተጨማሪ ብስራት የሆነውን እጅግ ዘመናዊ አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ሕንፃ ግንባታ አጠናቅቀን፤ መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
በአይነቱ የመጀመሪያ እና እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ መርቀን ብዙም ሳንቆይ፣ ዓለም በፊልም ኢንዱስትሪው የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ በያዝነው ዕቅድ መሰረት፣ ለኪነ-ጥበብና ለከያኒያን ትልቅ የምስራች የሆነውን አዲስ እና እጅግ ዘመናዊ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ሕንፃ በዛሬው ዕለት ሥራ አስጀምረናል ብለዋል።
 
አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ሕንፃ፣ ባለ15 ወለል ሲሆን፤ የሕንፃው አጠቃላይ ስፋት 24 ሺ ካሬ ሜትር ሆኖ ባለ አራት ወለል የመኪና ማቆሚያን የያዘ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
592 ሕፃናትንና 887 አዋቂዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት የሲኒማ አዳራሾችን ጨምሮ በቂ የሆነ የድምፅ ማስተላለፊያ ሲስተም፣ ዘመናዊ የመብራት ስርጭት፣ የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን ማካተቱንም አመላክተዋል።
በተጨማሪም፤ ለቢሮዎች፣ ለስቱዲዮ፣ ለሥዕል እና አርት ጋለሪ፣ ለቤተ-መፃሕፍት እና ለተለያዩ ተያያዠ አገልግሎቶች፣ ለካፍቴሪያ፣ ለሱፐርማኬት፣ ለምግብ ቤት፣ ለሱቆች፣ ለውበት ሳሎን፣ ለባንክ አገልግሎት፣ የትኬት መሸጫ ቢሮዎች እና ለጉብኝት አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችንም አሟልቷል ብለዋል።
በቅጥር ጊቢውም የልጆች መጫወቻ የስፖርት ሜዳ፣ የመኪና ማቆሚያና አረንጓዴ ስፍራዎችን ጨምሮ ለማስታወቂያ የሚሆኑ ስክሪኖች እና ዘመናዊ ሊፍቶች እንዲሁም የፓርኪንግ ቴክኖሎጂዎች እንደተገጠሙለት አስታውቀዋል።
በዚህ አዲስና ዘመናዊ ለትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ሥራ ላይ የተሳተፋችሁ አማካሪዎች፣ ተቋራጮች እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ አመራሮች እና ሰራተኞች፣ ደከመን ሰለቸን ሳትሉ የተሳተፋችሁትን በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ እና በራሴ ስም ላመሰግናችሁ እውዳለሁ ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡