በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሰባት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች ከ28 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውና የክልሉ የደን ሽፋን 29 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሰው ልጅ ሕይወት ከተፈጥሮ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑንና የተፈጥሮን ሚዛን ጠብቆ ማቆየት የሰው ልጅ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሞ ሕዝብ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የመኖርን ጥበብ በገዳ ሥርዓት ደንግጎ ለዘመናት ያቆየው እሴት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ከእነዚህ ጥንታዊ እሴቶች መራቅ ግን ተራራዎችን፣ ሸለቆዎችንና ወንዞችን በማድረቅ ለከባድ የአየር ንብረት ለውጥና ለድርቅ ፈተና አጋልጦን መቆየቱን አንስተዋል።
ይህንን ፈተና ለመቀልበስ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተቀረጸውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቁርጠኝነት ወደ ተግባር በመቀየር ታላላቅ ስኬቶችን ማስመዝገቡን አቶ ሽመልስ ይፋ አድርገዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ማኅበረሰቡን በማሳተፍ በተሠራ ጠንካራ ሥራ ከ28 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶች የተተከሉ ሲሆን፣ በተደረገላቸው ቀጣይነት ያለው እንክብካቤና ጥበቃ 85 በመቶ የሚሆኑት መጽደቅ ችለዋል።
በዚህ ታሪካዊ ውጤት አማካኝነት የኦሮሚያ ክልል የደን ሽፋን ከነበረበት 17 በመቶ ወደ 29 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል። ይህ ስኬት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2030 የደን ሽፋኗን ከ30 በመቶ በላይ ለማድረስ የያዘችውን ብሔራዊ ዕቅድ፣ የኦሮሚያ ክልል አስቀድሞ ለማሳካት ትልቅ መነሻ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ የተመዘገበው ድል በኦሮሚያ ላይ ተከስቶ የነበረውን የድርቅ ታሪክ የለወጠና የደረቁ ሸለቆዎችንና ተራራዎችን መልሶ ያለመለመ የሕዝቡ የሁለንተናዊ ድካም ውጤት በመሆኑ፣ ክልላዊ መንግሥቱ ለሕዝቡ የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል።
የኦሮሚያ ክልል የያዘውን አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት፣ የውኃ ምንጮችንና ግድቦችን ደኅንነት የማስጠበቅ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ግብ ይበልጥ ለማፋጠን በዘንድሮው ዓመት ታላቅ ዕቅድ መያዙን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
በነገው ዕለት በሚካሄደው ክልላዊ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ መላው የክልሉ ሕዝብ በጋራና በግል በነቂስ ወጥቶ የችግኝ ተከላ ሥራውን በይፋ እንዲጀምር ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ተስፋችንን እንትከል" በማለት ያስተላለፉትን ጥሪ ከግብ ለማድረስ በቁጭት የሚሠራበት መሆኑን በመጠቆም፣ እያንዳንዱ ዜጋ የነገዋን ሀገር አረንጓዴ ለማድረግና የትውልድ ጥላን ዛሬ ለመገንባት የበኩሉን ብሔራዊ ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በሃይማኖት ከበደ