ዛሬ ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የመጣውን የሙቀት መጨመር፣ የሰደድ እሳት፣ የጎርፍ እንዲሁም የድርቅ አደጋዎችን ለመቋቋም በብርቱ ትግል ውስጥ ትገኛለች።
አፍሪካ ለዓለም የሙቀት መጨመር ያበረከተችው አስተዋጽኦ እጅግ አነስተኛ ቢሆንም፣ የችግሩ ቀዳሚ ተጠቂ መሆኗ አልቀረም።
ኢትዮጵያ ይህንን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቀነስ ተግባራዊ እርምጃ በመውሰድ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተስፋን ማለምና ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር እያሳየች ትገኛለች።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው "የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር" በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ ስኬት ብቻ መሆኑ አብቅቶ፣ ለመላው የአፍሪካ አህጉር ብሩህ የተስፋ ስንቅና ታላቅ የተሞክሮ ምንጭ ለመሆን በቅቷል።
መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በመላው ኢትዮጵያ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ ይህም የሀገራችንን የደን ሽፋን በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 17.2 በመቶ በአሁኑ ወቅት ወደ 23.6 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
በዘንድሮው የችግኝ ተከላ ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን የ65 ቢሊዮን ታሪካዊ ግብ ለማሳካት በሚያስችል መልኩ ከ8 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ዝግጁ ተደርገዋል።
ይህ ዓይነቱ መጠነ-ሰፊ ንቅናቄ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ፣ የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
መርሐ ግብሩ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ ከማድረጉ ባሻገር፣ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና አፕል ያሉ ለምግብነትና ለገበያ የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት አካትቷል።
ይህም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ “ከምድር ጥበቃ ወደ ማዕድ በረከት” የተሻገረ ስትራቴጂ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ሲያስጀምሩ የነበራቸው ራዕይ በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ አልነበረም።
የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር የለሽ በመሆኑ፣ መከላከል የሚቻለውም በጋራና በትብብር ሲሰራ ብቻ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ የቀጣናውን በረሃማነት በጋራ ለመግታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት ማለትም ለጂቡቲ፣ ለደቡብ ሱዳንና ለኬንያ አበርክታለች።
ይህ ተግባር የፓን-አፍሪካኒዝም እሴትን በተግባር ያሳየ፣ ለመላው አፍሪካውያን አንድነትና አብሮነት አዲስ ትርጉም የሰጠ አርዓያነት ያለው ስኬት ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው አቅም፣ በጋራና በትብብር መፍታት እንደሚችሉ ያሳዩበት ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ኢትዮጵያ ያበሰረችው የአረንጓዴ ተስፋ ብርሃን አህጉሪቱን ከተጋረጠባት የበረሃማነትና የአየር ንብረት መዛባት አደጋ ታድጎ፣ የነገዋን አፍሪካ ውብና ለምለም ለማድረግ የበኩሉን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።
በላሉ ኢታላ