Search

“አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ የተገለጠችበት ደማቅ ብሔራዊ ቀለም ነው”፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

እሑድ ሰኔ 21, 2018 49

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከእሳቤ እስከ ትግበራው ድረስ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ የተገለጠችበት ደማቅ ብሔራዊ ቀለሟ መሆኑን ገልጸዋል።

የታላላቅ ሥልጣኔዎች እና የነጠሩ እውቀቶች ማኅደር በሆነችው ኢትዮጵያ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ እሳቤ፥ የአሁኑ ትውልድ የአርቆ አሳቢ አባቶቹ እውነተኛ ልጅ መሆኑን ያስመሰከረበት የጠራ ሐቅ ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል በተለምዶ ከምናየው ተደጋጋሚ የኮንፍረንስ ዕቅድ በተሻገረ መልኩ፣ አፈር ነክቶና ጭቃ ረግጦ በትጋት በመሥራት የሚመጣ ውጤት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሐሳብ ከማመንጨት ጀምሮ እስከ ትግበራው ድረስ ግንባር ቀደም ሆነው በተግባር ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

ይህ የጠራ ዕቅድና መዳረሻ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ፕሮጀክት ከታዳጊ ሕፃናት ጀምሮ እስከ አረጋውያን ድረስ የተሳተፉበት ታሪካዊ የልማት ዘመቻ መሆኑን አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ልጆች ለዓመታት በስኬት የገነቡት ይህ ኢኒሼቲቭ ሀገራችንን በዓለም ፊት በክብር እያስጠራ ያለ የለውጥ ምልክት ሆኗል ብለዋል።

እንደ ኮፕ 32 (COP 32) ያሉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮችን የማስተናገድ ዕድሎችም በተባበረ ክንድ እና በተደመረ እሳቤ የመሥራታችን ውጤቶች እንዲሁም የብሔራዊ ዐሻራችን ታላቅ ሽልማቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌሎች የለውጥ ግቦች የታዩ የትጋት ድል ፍሬዎች በተደመሩ ጥረቶች ኢትዮጵያ በእርግጥም እያለማችና እየፈካች መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በሁሉም መስክ አቅደን የምንተገብራቸው ሀገራዊ ሕልሞቻችን እስኪሳኩ ድረስ በብርታት መሥራታችንን እንቀጥላለን ሲሉተስፋን እንትከል!” የሚለውን ጥሪ በድጋሚ አስተላልፈዋል።