በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ሀቅ ይዞ በመሞገት የሚታወቀው መሐመድ አል አሩሲ በኢቲቪ “ስለ ሀገር” መሰናዶ ላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ፍጹም ሰላማዊ መሆኑን አስገንዝቧል።
ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ታላቅ ሀገር በባሕር በር እጥረት ታፍና ልትቀጥል እንደማትችል የጠቀሰው አል አሩሲ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሌሎችን ሉዓላዊነት ለመንካት አለመሆኑኑንም ተናግሯል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግጋትንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሪያዎችን በመጠቀም፣ ከጎረቤቶቿ ጋር በውይይትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርቶ የሚከናወን ስኬታማ ጉዞ መሆኑን አስረድቷል።
እንደ ግብፅ ያሉ የማይመለከታቸው ሀገራት የራሳቸው ባሕር የተነካ አስመስለው የሚያቀርቡት ተቃውሞ፣ ዓላማው ኢትዮጵያን ሁልጊዜ በባሕር በር አማካኝነት አስሮ ለማስቀመጥና ሉዓላዊነቷን ለማስገደድ ካላቸው የቆየ ፍላጎት የመነጨ መሆኑን አል አሩሲ አጋልጧል።
“ለኢትዮጵያውያን ቀይ ባሕር እና የህዳሴው ግድብ የተለያዩ አይደሉም፤ ሁለቱም ብሔራዊ ደኅንነታችን፣ ሉዓላዊነታችንና ታሪካዊ ማንነታችን ናቸው” ያለው አል አሩሲ፤ ዜጎች ለሕዳሴው ግድብ በጋራ እንደቆሙት ሁሉ አሁን ለተጀመረውና ፍሬ እያፈራ ለሚገኘው የባሕር በር ጥያቄም ከመንግሥት ጎን በፅናት ሊቆሙ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።
ማሸነፍ በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በእውነት፣ በፖለቲካና በጂኦግራፊ ጭምር መሆኑን በመጥቀስም ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ቀይ መስመሯን አሳልፋ እንደማትሰጥ አስታውቋል።
በአረብኛና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሀገር ላይ የሚሰነዘሩ የውሸት አጀንዳዎችን የመመከትና የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም የማሰማት ተጋድሎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ሀገር ለማንቋሸሽ ከጠላቶች ጎን መቆማቸው ቢያሳዝንም፣ የውስጥ ገመናን ጠብቆ በእውነት መሟገት እንደሚገባ አሳስቧል።
ከጎረቤት ሕዝቦች ጋር ምንም ዓይነት ችግር ባይኖርም በኢትዮጵያ ላይ ክፋትን የሚያስቡ የውጭ አካላትና የሀገር ውስጥ ባንዳዎች ግን ወደፊት ዋጋ እንደሚከፍሉ አስታውቋል።
በመሐመድ ፊጣሞ