በብራዚሏ የወደብ ከተማ ቤሌም በሚካሄደው የዓለም አየር ንብረት ጉባዔ(COP30) የዓለም ሙቀት መጨመር ጉዳት ካደረሰባቸው ሀገራት ድምጾች እየተሰሙ ናቸው።
ትላንት በተካሄደው የመሪዎቹ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የሄይቲ ዲፕሎማት ስሚዝ አውጉስቲን "ሀሪኬን ሜሊሳ" የተባለው አውሎ ነፋስ ሀገራቸውን ማውደሙን ጠቅሰው፣ አነስተኛ ደሴቶች የችግሩ ዋነኛ ተጠያቂ እየሆኑ ናቸው ብለዋል።
የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኪቱሬ ኪንዲኪ በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ገዳይ የመሬት መንሸራተት በሀገራቸው መከሰቱን ጠቁመው፤ ቀደም ሲል በምዕተ ዓመት አንድ ጊዜ ይከሰት የነበረው ከፍተኛ ድርቅ ከአውዳሚ ጎርፍ ጋር እየተፈራረቀ ሕይወትን ማጥፋቱን ቀጥሏል ብለዋል።
የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ፥ በ2022 በግብፅ በተካሄደው ኮንፈረንስ የተቋቋመው የኪሳራ እና የጉዳት ፈንድ የሚጠበቀውን ያክል አለመሥራቱን ጠቅሰው፤ ቃላቸውን ያላከበሩ መሪዎች ሊያፍሩ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ የሱፍ በበኩላቸው አፍሪካ የአየር ንብረት ፍትሕን እንጂ እርዳታ እየጠየቀች እንዳልሆነች ጠቅሰው፤ ዓለም ወደ ተግባራዊ ውሳኔ መምጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
የጉባዔው አስተናጋጅ ሀገር ብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ፥ የደን ጭፍጨፋን ለመቀልበስ፣ የነዳጅ አጠቃቀምን ለማሻሻል እና አስፈላጊውን ሀብት ለማሰባሰብ ተጨባጭ ፍኖተ ካርታ እንደሚያስፈልግ በአፅንዖት ገልጸዋል።
የጋራ ዓለም አቀፍ የካርቦን ገበያን በማጠናከር በካይ ጋዝን በማመንጨት ብዙም አስተዋጽኦ የማያደርጉ ሀገራት ከፍተኛ ልቀትን ከሚያመነጩ ሀገራት የካርቦን ሽያጭ ፋይናንስ የሚያገኙበት እርምጃም እንዲጠናከር ተጠይቋል።
#EBC #ebcdotstream #climatechange #UN #COP30 #belem #brazil