Search

ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለማስተናገድ ይፋዊ ጥያቄ አቀረበች

ዓርብ ጥቅምት 28, 2018 28

ኢትዮጵያ በብራዚል እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP30) ላይ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለማስተናገድ ይፋዊ ጥያቄ አቀረበች።
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት በብራዚል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ፤ የዓለም ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የገቡትን ቃል ለማክበር ፍላጎታቸው አናሳ በሆነበት በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ምሳሌ የሚሆን ተግባር መፈጸሟን ገልጸዋል።
 
 
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት የረጅም ጊዜ ልምድ እና የላቀ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እንደአላት ጠቁመው፤ በተጨማሪም ከ160 በላይ ለሆኑ የዲፕሎማቲክ ተቋማት ጽህፈት ቤቶች መቀመጫ መሆኗንም አስረድተዋል።
32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ልምዱም አቅሙም እንዳላት ገልጸው፣ ሀገራት ድጋፍ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
 
በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያን አቋምና ፍላጎት ያቀረቡት አምባሳደሩ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረውን የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲሁም ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያግዙ ተግባራዊ ሥራዎችን ያከናወነችው ኢትዮጵያ፣ ጉባኤውን ለማስተናገድ ፍላጎቱም ዝግጁነቱም አላት ብለዋል።
አዲስ አበባ በተካሄደውን በ2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል ያሉት አምባሳደሩ፤ በጉዳዩ ላይ ሁሉም ቁርጠኛ መሆን እንደአለበትም አመላክተዋል።
 
በሀብታሙ ተክለስላሴ