Search

ፍትሕን እንጂ እርዳታን እየጠየቅን አይደለም:- የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበር

ዓርብ ጥቅምት 28, 2018 51

አፍሪካ፣ የአየር ንብረት ፍትሕን እንጂ እርዳታ እየጠየቀች እንዳልሆነ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ተናገሩ።

ሊቀመንበሩ በቤለም የመሪዎች ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ አፍሪካ በ30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ (COP30) ላይ ስትሳተፍ በአየር ንብረት ጉዳይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ በመሻት እና ለዚያም ራሷን አዘጋጅታ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

"የአህጉሪቱ ወጣቶች ፈጠራ ታክሎባቸው ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ የፀሐይ እና የውኃ የኃይል ልማቶች አፍሪካ ፍትሐዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዝቅተኛ የካርቦን አመንጪ የኃይል አማራጮችን በመፍጠር የዓለምን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እያመላከተች ነው" ብለዋል።

ይሁን እንጂ የዓለምን 40 በመቶ ታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላት አፍሪካ ከ12 በመቶ በታች የአየር ንብረት ፋይናንስ እንደምታገኝ ነው የጠቆሙት።

አክለውም፣ "እየጠየቅን ያለነው በጎ አድራጎት ሳይሆን የአየር ንብረት ፍትሕን፤ ፍትሐዊ ፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ዕድልን ነው፤ ለአየር ንብረት ቀውስ አነስተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሀገራት ከባዱን ሸክም መሸከም የለባቸውም" ብለዋል።

30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ (COP30) ቃል ኪዳኖች ወደ ተግባር ተለውጠው ዓለም ወደ ተጨባጭ የጋራ ፍትሕ እና ብልፅግና የምትሸጋገርበት ዕድል የሚፈጠርበት መድረክ እንዲሆን ጠይቀዋል።

"የከፊል እርምጃ ጊዜው አልፏል" ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ደፋር እና የተባበረ ተግባራዊ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜው አሁን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ (COP30) ከኅዳር 01 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በብራዚሏ የወደብ ከተማ ቤለም የሚካሄድ ይሆናል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #EBCdotstream #COP30 #Brazil #climatechange #belem