Search

ከ400 ዓመታት በኋላ ጎንደር ትንሣኤዋን እያየች ነው - አፈ-ጉባዔ አገኘው ተሻገር

ቅዳሜ ጥቅምት 29, 2018 39

በኢትዮጵያ የመንግሥት ምስረታ ሂደት ውስጥ ጥንታዊ ከሆኑ ከተማዎች መካከል የሆነችው ጎንደር፥ አሁን እየተሰሩላት ያሉ የልማት ሥራዎች የጎንደርን ትንሣኤ 400 ዓመታት በኋላ የሚያሳዩ እንደሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ አገኘው ተሻገር ተናገሩ።

ፋሲል ተጠገነ አይደለም የሚባለው እንደገና ተሰራ እንጂ ያሉት አፈ ጉባዔው፥ ለዚህ ደግሞ የትም መሄድ አያስፈልግም እኛን መጠየቅ በቂ ነው ብለዋል።

ጎንደርን ዛሬ አይደለም የማውቃት ያሉት አፈ ጉባዔው ተወልደን እስከ ማደግ፤ በተለያዩ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሆነን እስከ ማገልገል ብንደርስም ጎንደር ያላትን ሀብት ከማወቅ ውጪ ገልጠን ማየት ተስኖን ነበር ብለዋል።

ከገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የጎርጎራ ፕሮጀክት ሌላኛው የጎንደርን ውበት አጉልቶ ያሳየ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው፥ እጅግ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሆነ ማየት እንደቻሉ ተናግረዋል።

በከተማዋ የተሰሩ የኮሪደር ልማቶች ጎንደር ጥንታዊነቷን ሳትለቅ የተሰሩ በመሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋልም ነው ያሉት።

የጣና ነሸ 2 ጀልባወደ ሥራ መግባቷ ደግሞ በጣና ሐይቅ ላይ የሚኖረውን የቱሪዝም እና የትራንስፖርት ዘርፍ በአግባቡ ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በሀ/ሚካኤል ክፍሉ