Search

ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ወሳኝ የሆነው ሀገራዊ የወል ትርክት

ቅዳሜ ጥቅምት 29, 2018 36

በኢትዮጵያ ሀገራዊ የወል ትርክትን በመገንባት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል።

የብዝኃ ባህል፣ ቅርስ እና ታሪክ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምድ የጋራ ትርክት መገንባት አስፈላጊ ስለመሆኑም በርካቶች ያነሳሉ።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ብዝኃነት መገለጫዋ የሆኑ ልዩ ልዩ ማሳያዎች አሏት ይላሉ።

ኢትዮጵያ ሕዝቦችን በጋራ ያስተሳሰረውን የዓድዋን ድል የአንድነቷ ምስክር አድርጋ የያዘች ሀገር ስለመሆኗም ገልጸው፤ የተዛቡ ትርክቶችን አንድ በሚያደርጉ የጋራ ትርክቶች መተካት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የተዛቡ ትርክቶች በአንድ ጀንበር የመጡ አይደሉም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የብዙ ዘመናት ችግር በመሆናቸው ችግሮቻችንን ፈትተን በጋራ ትርክት ላይ ለመሥራት የሚያስችሉ ጥረቶች ተጀምረዋል ሲሉ አስረድተዋል።

ገዥ ትርክትን በመገንባትም የሀገር ግንባታ ጉዞን ማሳለጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የታሪክ መምህር የሆኑት በላይ ስጦታው በበኩላቸው፤ ታሪክን መሠረት አድርጎ የጋራ ትርክትን በመገንባት ሀገርን ማሳደግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያውያን ዓለም ያወቀው አኩሪ ታሪክ እያለን አንዳንድ ጸሐፊያን ግን ነጠላ ትርክት ላይ ያተኮረ ጽሑፍ ያዘጋጃሉ ሲሉ አንስተዋል።

ይህ አካሄድ ትክክል አለመሆኑንም አመላክተው፤ አሰባሳቢ ትርክቶችን በማጎልበት ለሀገር ብልፅግና ልንተባበር ይገባል ብለዋል።

አሰባሳቢ የወል ትርክት ለሀገር ግንባታ ወሳኝ በመሆኑም ገንቢ ትርክቶችን በመጠቀም ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ዕድገት የሚተጋበትን መንገድ ማመላከት እንደሚገባም አስረድተዋል።

በሜሮን ንብረት

#EBC #ebcdotstream #united #Ethiopia